ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ስለ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የተናገሩት ነው ተብሎ የተሰራጨው ቪድዮ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተቀናበረ ነው
መስከረም 24፣ 2018
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አማካኝነት እየተቀናበሩ በዋነኝነት ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።
እነዚህ በረቀቀ መልኩ በቪድዮ፣ በድምፅ እና በምስል ተቀናብረው የሚቀርቡ ስራዎች አንዳንዶቹ ለቀልድ/ስላቅ ተብለው የሚሰሩ ቢሆንም አንዳንዶቹ ሆን ተብሎ ሰዎችን ለማሳሳት እና በዛውም እንደ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ያሉ ጥቅሞች ለማግኘት ታልመው የሚሰራጩ ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ኢትዮጵያን እና ጠ/ሚር አብይ አህመድን በተመለከተ ተናግረውታል የተባለ ቪድዮ እየተሰራጨ መሆኑን ተመልክተናል።
የ46 ሰከንድ ርዝመት ያለው ቪድዮ ላይ ትረምፕ “ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ… [በጠ/ሚር አብይ] ላይ እንተማመናለን። የተጀመሩትን በማፋጠን እና በትናንሽ እና መለስተኛ ዘርፎች ላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ በጭስ አልባ ኢንደስትሪው ዘርፍ የሚያስገርም ስራ እየሰራ ነው። ቆንጆ እና ንፁህ ሀገር እየመሩ ያሉ መሪ ናቸው” ሲሉ ይደመጣል (ሊንክ: https://www.facebook.com/share/v/1AMjztUkQZ/)
ቪድዮውን ፌስቡክ ላይ ካጋሩት መሀል ‘Qabsaawa Finfinnee’ የተባለ ከ61 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ይገኝበታል። ይህ የፌስቡክ ማረጋገጫ (blue badge) ያለው ገፅ ያሰራጨው ቪድዮ ከ400 በላይ ግብረ መልስ ያገኘ ሲሆን ከ8,500 በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
ኢትዮጵያ ቼክ የቪድዮውን ትክክለኛነት በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ከተከታታዮቹ ደርሰውታል።
በዚህ ቪድዮ ዙርያ ባደረግነው ማጣራት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ይህንን ንግግር በፍፁም እንዳላደረጉ እና ቪድዮው ከትክክለኛ ንግግድ ተወስዶ፣ ድምፁም በቅንብር እንዲገባ ተደርጎ የተመረተ ቪድዮ መሆኑን መመልከት ችለናል።
ትክክለኛው ቪድዮ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ አንድ አውሮፕላን እና ሄሊኮፕተር ዋሽንግተን አቅራቢያ ተጋጭተው የበርካቶች ህይወት ካለፈ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተወሰደ ነው (ሊንክ: https://www.youtube.com/live/ShRYdYTtIx8?si=lieX_73Nh6SGhhsO)
እዚህ ቪድዮ ላይ ፕሬዝደንቱ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲናገሩ አይሰማም። በተጨማሪም በርካታ የድረ-ገፅ አሰሳ ያደረግን ሲሆን ፕሬዝደንት ትረምፕ ይህን ንግግር እንዳደረጉ የሚያስረዳ አንድም መረጃ አልተገኘም።
በቅንብር ተሰርተው የሚሰራጩ መረጃዎች ለሀሰተኛ መረጃ ስለሚያጋልጡን ጥንቃቄ አይለየን።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::