ሜታ የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከታተል ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ክራውድታንግልን ከስራ ውጭ ማድረጉን አስታወቀ

ነሐሴ 10፣ 2016
1. ሜታ ጋዜጠኞች፣ መረጃ አጣሪዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከታተል ይጠቀሙበት የነበረው ክራውድታንግል (CrowdTangle) የተባለውን መገልገያ ከስራ ውጭ ማድረጉን አስታውቋል። ሜታ ዛሬ ባስነበበው አጭር መግለጫ መገልገያው ካለፈው ዕረቡ ጀምሮ አገልግሎቱ መቋረጡን የገለጸ ሲሆን ደንበኞቹ በምትኩም ሜታ ኮንቴንት ላይበራሪ (Meta Content Library) እና ኮንቴንት ላይበራሪ ኤፒአይ (Content Library API) የተሰኙ መገልገያዎችን መጠቀም እንደሚችሉ አስገንዝቧል። ይህን ውሳኔ የአውሮፓ ኮሚሽንን ጨምሮ ብዙዎች ተቃውመውታል። በተኪነት የቀረቡት መገልገያዎች ከክራውድታንግል አንጻር በርካታ ውስንነቶች እንዳሉባቸውም በማንሳት ባለሙያዎች ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
2. የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር እና የሚመሩት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በውህዳን ማህበረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ንግግሮችን በተደጋጋሚ አሰምተዋል ሲል ሂውማን ራይትስ ዋች በሳምንቱ አጋማሽ ባወጣው ሪፖርት ከሷል። አለማቀፉ የሰብዐዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት የመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ጠቅላይ ሚንስትሩ ካደረጓቸው 173 ንግግሮች መካከል 110ሩ ጥላቻ አዘል መሆናቸውን መዝግቢያለሁ ብሏል። በአለማችን ትልቁን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በመከወን የምቻወቀው ህንድ ባሳለፍነው ግንቦት ወር የማጠቃለያ ምርጫ ማድረጓ ይታወቃል።
3. ቴሌግራም ይዘት ፈጣሪዎች (Content Creaters) ለስራቸው ገንዘብ የሚያገኙበትን አሰራር መጀመሩን ዕረቡ ዕለት አስታውቋል። ቴሌግራም ባስነበበው መግለጫ ይዘት ፈጣሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር የደንበኝነት ክፍያን (Subscription) እንዲሁም ስጦታን (Star Reaction) ያማከለ እንደሚሆን አብራርቷል። በላላ ቁጭሩ በክፉ የሚነሳው ቴሌግራም ይዘት ፈጣሪዎችን ለመጥቀም ማሰቡን ይፋ ያደረገው ስራ የጀመረበትን 11ኛ አመት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ነው።
በሳምንቱ ያቀረብናቸው መረጃዎች የቴሌግራም ሊንኮች:
-በሰኞ መልዕክታችን የማህበራዊ ሚዲያ ኣአጠቃቀም ስነምግባርን የተመለከተ ጽሁፍ በትግርኛ አስነብበናል:
https://t.me/ethiopiacheck/2409
-እንዲሁም በትግራይ ክልል አስቸኳይ ጊዜ ኣአዋጅ ታውጇል ወይ ለሚሉ ጥያቄዎች ማብራሪያ አቅርበናል:
https://t.me/ethiopiacheck/2410
-በአፍሪካ ህብረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ዙርያ ማህበራዊ ሚድያ ላይ ስለተሰራጨው መረጃ መንግስት የሰጠውን ምላሽም አጋርተናል:
https://t.me/ethiopiacheck/2411
-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ይልቅ ወደ አስመራ ለሚደረግ ጉዞ የበለጠ ትኬት ዋጋ እንደሚያስከፍል በመግለጽ የተሰራጩ መረጃዎችንም ፈትሸናል: https://t.me/ethiopiacheck/2413
-ከረጅም ቪድዮዎች ላይ ተቆርጠው የሚጋሩ አጠር ያሉ ክሊፖች ለተሳሳተ መረጃ እንዳያጋልጡን ማድረግ ስላለብን ጥንቃቄም ማብራሪያ አቅርበናል: https://t.me/ethiopiacheck/2415
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
