ጠ/ሚር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት መዳረሻነት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ስለመሆኗ ስላነሱት ሀሳብ ጥናቶች ምን ይላሉ?
ጥቅምት 21፣ 2017 ዓ.ም
ጠ/ሚር አብይ አህመድ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መሀል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመሯጯ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ነበር።
“በአፍሪካ ውስጥ የፈለገው ያህል የሚድያ ፕሮፖጋንዳው ቢስፋፋም ኢትዮጵያን የሚያክል ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚባል ሀገር እምብዛም የለም” በማለት የተናገሩት ይህም ከመሬት አጠቃቀም፣ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም ዝቅተኛ የብልሹ አሰራር/ጉቦኝነት መኖርን አንስተዋል።
በዚህ ዙርያ በአፍሪካ በየአመቱ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሆኑ መዳረሻዎችን በማውጣት የሚታወቀው ግዙፉ RMB ግሩፕ ያወጣውን ጥናት እንመልከት።
የዘንድሮው (እአአ የ2024) የተቋሙ ጥናት እንደሚያሳየው ሲሸልስ ቀዳሚዋ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር ስትሆን በምክንያትነት የተቀመጠው ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር፣ የህዝብ እድገት እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ናቸው።
በሁለተኝነት የተቀመጠችው ሞሪሺየስ ስትሆን ሀገሪቱ ደግሞ በፈጠራ፣ በኢኖሚ ነፃነት፣ በጥሩ መልኩ በሚመራ የኢንቨስትመንት ሴክተር እና ከፍ ባለ የነፍስ ወከፍ ገቢ ተመራጭ ሆናለች።
ከሶስት እስከ አምስት ያለውን ቦታ የያዙት ደግሞ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ናቸው።
RMB የግዙፉ የደቡብ አፍሪካው ፈርስት ራንድ ግሩፕ የኮርፖሬት እና ኢንቨስትመንት ባንኪንግ (CIB) ቅርንጫፍ ሲሆን ሪፖርቱን በዚህ ሊንክ መመልከት ይቻላል: https://www.rmb.co.za/where-to-invest-in-africa-2024
በዚህ ዙርያ አለም አቀፍ ሚድያዎች ዘገባዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን የፋይናንስ ዜናዎችን በማውጣት የሚታወቀው ብሉምበርግ የሰራውን ዜናም መመልከት ይቻላል: https://www.bloomberg.com/news/articles/2024-08-06/island-nations-top-egypt-as-best-african-investment-destinations?embedded-checkout=true
ከዚህ ተቋም በተጨማሪ የሌሎች ሁለት ድርጅቶችን ጥናት የተመለከትን ሲሆን ኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት እንጂ አሁን ላይ በአንደኝነት ተመራጭ ከሚባሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን አያሳዩም።
በዚህም ምክንያት ይህን በፓርላማ የቀረበ ንግግር ተጋኖ የቀረበ መሆኑን ተመልክተናል።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::