ኢንፊኒቲ ፓወር’ የተባለውን አለም አቀፍ የኢነርጂ ኩባንያን ስም በመጠቀም እየተከናወነ የሚገኝ የማጭበርበር ድርጊት 

ሀምሌ 14፣ 2016 ዓ.ም

‘ኢንፊኒቲ ፓወር’ ከተባለው ግዙፍ የኢነርጂ ኩባንያ ጋር የሚሰሩ በማስመሰል በርከት ያሉ የቴሌግራም፣ የፌስቡክ፣ የዩትዩብ እና የቲክቶክ አካውንቶች ‘ተቀላቀሉንና ትርፋማ ይሁኑ’ የሚሉ ጥሪዎችን በስፋት በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል። የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም እየቀረበ ያለውን ጥሪ እንድናጣራላቸው ጠይቀውናል።

እነዚህ ጥሪ አቅራቢዎች ዋና መስሪያ ቤቱን ግብጽ በማድረግ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በታዳሽ ሀይል ልማት ላይ የሚሳተፈው ግዙፉ ኢንፊኒቲ ፓወር ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚገልጹ ሲሆን ድርጅቱም የሶላር ፓናሎችንና ተያያዥ ቁሳቁሶችን እንደሚገዛና እንደሚከራይ ያስነግራሉ፣ ይህም እጅግ ጠቀም ያለ ትርፍ እንደሚያስገኝ ይገልጻሉ።

በዕድሉ ለመጠቀምም ጥሪ አቅራቢዎቹ የሚሰጡትን ማስፈንጠሪያ በመከተል መመዝገብ እንዲሁም ክፍያ መፈጽም እንደሚገባም ያግባባሉ፣ እንዲሁም ክፍያ የተከፈለበትን ደረሰኝ በ 0989845159 ስልክ ቁጥር ወደተከፈተ የቴሌግራም አካውንት እንዲላክም ይጠይቃሉ።

የጉዳዩን ትክክለኛነት ለማወቅ ኢትዮጵያ ቼክ አለም አቀፉን ኢንፊኒቲ ፓወር የኢነርጂ ኩባንያ ያነጋጋረ ሲሆን ከላይ በተጠቀሱት የማህበራዊ ሚዲያዎች እየቀረበ ያለው ጥሪ ከእነሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና የማጭበርበር ድርጊት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ለምዝገባና ለክፍያ አገልግሎቶች እየዋለ ያለውም ድረገጽ የእነሱ አለመሆኑን አስታወቀዋል። በተጨማሪም ኩባንያው ጉዳዩን ወደህግ ሊወስደው እንደሚችል ጠቁሟል።

የኢንፊኒቲ ፓወር ትክክለኛ ድረገጽ የሚከተለው ብቻ መሆኑንም አስታውቋል: https://weareinfinitypower.com/

በማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች አማካኝነት በሚሰራጩ የማጭበርበር ድርጊቶች ሰለባ ላለመሆን ጥንቃቄ እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::