ከረጅም ቪድዮዎች ላይ ተቆርጠው የሚጋሩ አጠር ያሉ ክሊፖች ለተሳሳተ መረጃ እንዳያጋልጡን እንጠንቀቅ
ነሐሴ 10፣ 2016
ብዙዎቻችን ረዘም ያሉ ቃለ ምልልሶችን፣ ውይይቶችን፣ መግለጫዎችን ወይም ሌሎች በቪዲዮ መልክ የሚቀርቡ ይዘቶችን ለመከታተል ሁኔታዎች ላይፈቅዱልን ይችላሉ። የጊዜ እጥረት፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ የኢንተርኔት ፍሰት ጥራት አልያም የአማራጭ መብዛት በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ይህን ክፍተት ለመሙላትም ከረጅም ቪዲዮዎች ላይ ተቀንጭበው የሚጋሩ አጠር ያሉ ክሊፖችን እንመለከታለን። ቲክቶክ፣ የፌስቡክ ጥቅሎች (Facebook Reels) እንዲሁም የዩትዩብ አጭር ቪድዮዎች (YouTube Shorts) ደግሞ ለዚህ ምቹ መዳረሻዎች ናቸው።
ሆኖም እንዲህ ያሉ ቅንጫቢ ቪዲዮዎች ሙሉ መልዕክቱን ከተገቢው አውድ ጋር ማስተላለፍ ስለማይችሉ ለተሳሳተ መረጃ ሊያጋልጡን ይችላሉ። ስለሆነም ከረጅም ቪዲዮዎች ተቆርጠው የሚጋሩ ይዘቶችን ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ማለት ጠቃሚ ይሆናል:
-ሙሉ አውዱን ለመረዳት እንሞክር: ለዚህም ቅንጫቢ ክሊፑ ተቆርጦ የወጣበትን ሙሉ ቪዲዮ መመልከት ወይም ሌላ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡን ወደሚችሉ ምንጮች ማምራት ይመከራል።
-ያጋራውን አካውንት እንገምግም: ቅንጫቢ ክሊፑን ያጋራው አካውንት ከዚህ በፊት የገነባው የታማኝነት ደረጃን መገምገም ጠቃሚ ነው። ይህም አካውንቱ ቅንጫቢ ክሊፑን ለምን አላማ እንዳጋራው ለመገመት ያስችለናል።
-የአርትዖ ቴክኒኩን እንመርምር: የተጋራውን አጭር ቪዲዮ በጥንቃቄ በመመልከት አቆራረጡንና አቀጣጠሉን በጥንቃቄ መመርመር ጠቃሚ ነው። ይህም ከሌላ ቦታ የተጨመረ ድምጽ ወይም ምስል ስለመኖሩ አልያም ሆን ተብሎ መልዕክቱን ለማዛባት ተቆርጠው የወጡ ቃላቶች ስለመኖራቸው ይነግረናል።
-ወደ መረጃ አጣሪ ገጾች እንሂድ፤ እንጠይቅ: በተጋራው ቅንጫቢ ክሊፕ የተመለከትነው መልዕክት ጥርጣሬ ካሳደረብን መረጃ ወደሚያጣሩ ገጾች በማምራት በጉዳዩ ላይ የሰሩት ፍተሻ መኖሩን መመልከት ወይም መልዕክቱን እንዲያጣሩልን መጠየቅ እውነታውን ለማወቅ ይረዳናል።
ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ልብ ማለት ብሎም የተለመዱ የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃ ማሰራጫ መንገዶችን ማወቅ በእጅጉ ይጠቅመናል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::