ተመሳስለው የሚከፈቱ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን ለመለየት እንዲችሉ እነዚህን ነጥቦች ያስተውሉ
መስከረም 20፣ 2017 ዓ.ም
ማህበራዊ ሚዲያን ሀሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት፣ የማጭበርበር ድርጊት ለመፈጽም፣ በተደራጀ ሁኔታ ተጽኖ ለመፍጠር እንዲሁም ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት የሚጠቀሙ በርካታ አካላት ስለመኖራቸው ብዙዎቻችን እናውቃለን።
ለዚህ አሉታዊ ድርጊታቸው ተመሳስለው የሚከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶችን መጠቀም ተመራጭ ዘዴያቸው መሆኑን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭዎች የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ይመሰክራሉ።
እርስዎም እንደዚህ ባሉ ሀሰተኛ አካውንቶች ተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ ከመከተለዎና መልዕክቶቻቸውን ከማጋራትዎ በፊት የሚከተሉትን ምርመራዋች ይከውኑ:
– በአካውንቱ የተጠቀሱ ማንነት ገላጭ መረጃዎችን ስምረት ይመርምሩ
አብዛኞቹ ተመሳስለው የሚከፈቱ ወይም ሀሰተኛ አካውንቶች ትክክለኛ መስለው ለመታየት ብዙ ይጥራሉ።
ለዚህም ከበድ ያለ ስም፣ የፕሮፋይል ምስል፣ የማንነት ገላጭ ጽሁፍ እንዲሁም የሚኖሩበትን ከተማ ጠቋሚ መረጃ ያስቀምጣሉ።
አካውንቱ በተቋም ስም የተከፈተ ከሆነ ደግሞ የንግድ ምልክት ወይም አርማ፣ አድራሻ እና የድረገጽ ማስፈንጠሪያ ያያይዛሉ።
ሆኖም አካውንቱ ስለማንነቱ የተሟላ መረጃ ሰጥቷል ብለን ማመንና መከተል የለብንም። ከላይ የተዘረዘሩት መረጃዎች እርስበርስ ስምረት እንዳላቸው መመርመር ይገባናል።
‘ስሙና ፎቶ የአንድ ሰው ነው?’ ‘የተያያዘው ማስፈንጠሪያ ይሰራል?’ ‘አድራሻ ትክክለኛ ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን መመርመርም አስፈላጊ ነው።
– የፕሮፋይል ምስላቸው እውነተኛ ስለመሆኑ ያጣሩ
ሀሰተኛ አካውንቶችን በቀላሉ ለመለየት ከሚረዱን ዘዴዎች መካከል የፕሮፋይል ምስላቸውን በጥንቃቄ መመልከት ዋነኛው ነው።
እንዲህ ያሉ አካውንቶች እውነተኛ ፊት ስለሌላቸው የሌላን ሰው ፎቶ መጠቀም ብቸኛ አማራጫቸው ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ ምስሎችን ይጠቀማሉ።
ስለሆነም የፕሮፋይል ምስሎችን በጥንቃቄ መመልከት ተገቢ ይሆናል።
እንዲሁም ጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች (Google Reverse Image Search)፣ ቲንአይ (Tineye)፣ ያንዴክስ (Yandex) እና ሌሎችን ሪቨርስ ኢሜጅ ፈላጊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የፎቶውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ መሞከር ይገባናል።
– አካውንቱ የተከፈተበትን ጊዜ ይመልከቱ
ብዙዎቹ ሀሠተኛ አካውንቶች በቅርብ የተከፈቱ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ሲሆን አንዳንዶቹ የቆዩም ሊሆኑ ይችላሉ።
ከወራት ወይንም ከሳምንታት በፊት የተከፈቱና ተሳትፏቸው ጎላ ያለ አካውንቶች ከሆኑ እውነተኛ ላይሆኑ ስለሚችሉ ይጠንቀቁ።
በአንጻሩ አካውንቶቹ ከዓመታት በፊት የተከፈቱ ከሆኑ ተጨማሪ ማጣራት ያድርጉ።
አካውንቶቹ ስም አለመቀየራቸውን፣ ተሳትፎ የሚያደርጉበት መጠን በጊዜ ሂደት አለመቀየሩን ወዘተ ይመርምሩ።
– የፕሮፋይል ስሙንና የአካውንቱን URL ስምረት ይመርምሩ
በአብዛኛው እውነተኛ አካውንቶች የፕሮፋይል ስማቸውና የአካውንት URL ስምረት ይኖረዋል። በአንጻሩ በርከት ያሉ ሀሠተኛ አካውንቶች ስማቸውን በየጊዜው የመቀያየር ልምድ ስላላቸው የፕሮፋይል ስማቸውና የአካውንት URL ስምረት የተዘባ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሀሠተኛነት የጠረጠሩት አካውንት የፕሮፋይል ስሙ ‘David Jhonson’ ከሆነና የአካውንቱ URL “facebook.com/Abebe-belay” የሚል ከሆነ ሀሠተኛ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ስለሚሆን ጥንቃቄ ማደርግ ተገቢ ነው።
በተጨማሪም የተከታዮቻቸውን ብዛትና ማንነት፣ የሚከተሏቸውን ሰዎችና ተቋማት ማንነት፣ የሚያጋሯቸው መልዕክቶች ጥራት ወዘተ ስለአካውንቱ እውነተኛነት ወይንም ሀሠተኛነት የሚነግረን ነገር ስለሚኖር በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::