ሰው መሰል ፊቶች (fake faces) ምንድን ናቸው? በምንስ መለየት ይቻላል?

ሰው መሰል ፊቶች

የካቲት 17፣2015

የዛሬ ሁለት አመት ገደማ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ዋልታ “ጆርጅ ቦልተን” ከሚል ሀሠተኛ የትዊተር አካውንት መረጃ ወስደው እንዳጋሩ ኢትዮጵያ ቼክ አጋልጦ ነበር። የ“ጆርጅ ቦልተን” አካውንት ኢትዮጵያ ቼክ ከዚህ በፊት ካጋለጣቸው ሀሠተኛ አካውንቶች በአንድ ነገር ይለያል: በፕሮፋይል ምስሉ።

የ”ጆርጅ ቦልተን” የፕሮፋይል ምስል thispersondoesnotexist.com በተባለ ሰው መሰል ፊት (fake face) አምራች ድረ-ገጽ የተፈጠረ ነው። ይህ ድረ-ገጽ ጄኔረቲቭ አድቨርሳሪያል ኔትዎርክስ (generative adversarial networks) የተባለ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን የድረ-ገጹ ጎብኝዎች ገጹን ባደሱ (refresh) ቁጥር አዲስ ሰው መሰል ፊት ያመርታል። በዚህ ቴክኖሎጅ የሚመረቱ ሀሠተኛ ፊቶች ለመለየት በሚያዳግት መልኩ ከእውነተኛው የሰው ልጅ ፊቶች ጋር ይመሳሰላሉ።

የ thispersondoesnotexist.com ድረ-ገጽ መስራች ፊሊፕ ዋንግ በአንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ድረ-ገጹን የከፈተው ሰዎች የአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ ቴክኖሎጅ የደረሰበት ደረጃ እንዲረዱ በማሰብ መሆኑን ገልጾ ነበር። ፊሊፕ ይህን ይበል እንጅ በድረ-ገጹ የሚመረቱ ፊቶች ሀሰተኛ አካውንቶችንና ቦቶችን ለመክፈት በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል። ለምሳሌ አሶሼትድ ፕሬስ ከወራት በፊት እንዳጋለጠው ጀሲካ የተባለች ሰው መሰል ፊት ተጠቃሚ የሊንክዲን አካውንት ባለቤት ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ትስስር እስከመፍጠር ደርሳ ነበር።

በተመሳሳይ የመረጃ ማንጠር ስራ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ግራፊካ እና የአትላንቲክ ካውንስል ዲጂታል ፎረንሲክ ምርምር ላብራቶሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ አካውንት ከፍተው የሚጠቀሙ ሰው መሰል ፊቶችን ማጋለጥ ችለዋል።

ይህ ማለት ግን ሰው መሰል ፊት የሚጠቀሙ ሀሰተኞችን መለየት ቀላል ነው ማለት አይደለም። ቀደም ባሉት ዓመታት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የሚመረቱ ሰው መሰል ፊቶችን ለመለየት በትኩረት መመልከት በቂ ነበር። የተዛነፈ የፊት ቅርጽ፣ ትኩረት አልባ አይኖች፣ የተፋለሰ ጸጉር፣ ያልተመጣጠኑ ጆሮዎች እና ሌሎች እንከኖችን መለያቸው ነበሩ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚመረቱ ሰው መሰል ፊቶች በእጅጉ እንከን አልባ እየሆኑ ስለመጡ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ሆነዋል። በፎቶሾፕ የተቀናበሩ እና ሀሰተኛ ምስሎችን ለመለየት የሚረዱ የፎቶ ፎረንሲክ እና የሪቨርስ ሰርች መገልገያዎችም እነዚህን ፊቶች ለመለየት እምብዛም አይረዱም።

የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ለጊዜው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጅ የሚመረቱ ሰው መሰል ፊቶች መኖራቸውን ማወቅና መጠንቀቅ ከሀሰተኞች ተጽዕኖ ለመጠበቅ ብቸኛው አማራጭ ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::