የሜታ ኩባንያን ሰማያዊ ማረጋገጫ በተመለከተ ከተጋራ አሳሳች መረጃ እንጠንቀቅ!

የካቲት 14፣2015

ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት የሜታ ኩባንያን ሰማያዊ ማረጋገጫ በተመለከተ አሳሳች መረጃ ማጋራቱን ተመልክተናል።
ዋልታ ትላንት የካቲት 13/2015 በፌስቡክ ገጹ እና ድረ-ገጹ ባጋራዉ ዜና “ሜታ ኩባንያ ሰማያዊ ማረጋገጫ ምልክት (Blue Badge) የሚጠቀሙ ደንበኞችን በየወሩ ማስከፈል ሊጀምር መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ አስታወቀ” ሲል ዘግቧል።
በተጨማሪም “ኩባንያው ለድረ-ገጽ ሰማያዊ ማረጋገጫ ምልክት ተጠቃሚዎች በወር 11.99 ዶላር እንዲሁም ለአፕል ኩባንያ ምርት ለሆኑ አይ.ኦ.ኤስ መተግበሪያዎች በወር 14.99 ዶላር ለማስከፈል መወሰኑን ገልጸዋል” ይላል ዘገባዉ።
ይሁን እንጂ ሜታ የተጠቀሰውን ክፍያ የሚያስከፍለዉ አዲስ የትክክለኛነት ማረጋገጭ (verification badge) ለሚፈልጉ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች መሆኑን ነው ያስታወቀዉ።
ሜታ ከቀናት በፊት በድረ-ገጹ ባወጣዉ መግለጫ ይህ አዲሱና ሜታ ቬሪፋይድ (Meta Verified) የተሰኘዉ አገልግሎት ከዚህ በፊት የትክክለኛነት ማረጋገጫ ማግኛ መስፈርቶችን አሟልተዉ የተረጋገጡ አካዉንቶችን እንደማይመለከት አስታዉቋል።
ይህም ክፍያዉ ሁሉንም የትክክለኛነት ማረጋገጫ (Verification Badge) ተጠቃሚዎች የሚመለከት ተደርጎ የቀረበዉ የዋልታ ዘገባ አሳሳች መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ስለ ሜታ ቬሪፋይድ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘዉ የሜታ መግለጫም በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://about.fb.com/…/testing-meta-verified-to-help…/
በሌላ በኩል ይህ ሜታ ቬሪፋይድ የተሰኘ አገልግሎት የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎቻ የፌስቡክ አና ኢንስታግራም ተደራሽነት የሚጨምር፤ በስማቸዉ ተመሳስለው የሚከፈቱ ሀሰተኛ አካዉንቶች እና ገጾችን የሚከላከል እና ተገልጋዮቹ አካዉንታቸዉን በተመለከተ እክል ሲገጥማቸዉ ከሜታ ሰራተኞች እገዛ ማግኘት የሚያሰችላቸዉ መሆኑን ኩባንያዉ አስታዉቋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::