የትዊተር ሰማያዊ ባጅ ክፍያ ጉዳይ እና ሌሎች የአርብ ዳሰሳ መረጃዎች

YouTube creators who violate guidelines can now take a class

ሚያዝያ 06፣ 2015

በዛሬው የአርብ ሳምንታዊ ዳሰሳችን “ትዊተር ቀደም ባሉት ጊዜያት በነጻ ሰማያዊ ባጅ የወሰዱ አካውንቶች ወደ ክፍያ ስርዐት የማይገቡ ከሆነ አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥ አስታውቋል” የሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲሁም በሳምንቱ ያቀረብናቸውን መረጃዎች አጠናቅረን እንዲህ አቅርበናል።

1. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሐን አገልግሎት ለኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ዋልታ በትናትናው ዕለት ዘግቧል። አገልግሎቱ ለኢሳት በሰጠው ማስጠንቀቂያ የቴሌቪዥን ጣቢያው የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1185/2012ን ስለመጣሱ የሚገልጽ ይገኝበታል። በጽሁፍ በተሰጠው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያም ኢሳት አሰራጭቷቸዋል የተባሉ ዘገባዎች በምሳሌነት ተጠቅሰዋል።

2. የአውስትራሊያዋ ኸፕበርን ሻየር ከተማ ከንቲባ የሆኑት ብሪያን ሁድ ቻትጅፒቲን (ChatGPT) ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨትና ስም በማጥፋት እንደሚከሱ መናገራቸውን ዩሮኒውስ ዘግቧል። ከንቲባው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሆነውን ቻትጅፒቲን ለመክሰስ የወሰኑት እርሳቸውን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃዎችን እንደሚመልስ ከከተማው ነዋሪዎች ከሰሙ በኃላ መሆኑን ተናግረዋል። ቻትጅፒቲ ከንቲባውን በተመለከተ ከሚሰጣቸው መረጃዎች መካከል ከዓመታት በፊት ሙስና በመቀበል ወንጀል ለእስር ተዳርገው እንደነበር የሚገልጽ የተሳሳተ መረጃ ይገኝበታል ተብሏል። የከንቲባው ጠበቆች የቻትጅፒቲ ባለቤት ለሆነው ኦፕንኤአይ (OpenAI) አቤቱታ ያስገቡ ሲሆን በ4 ሳምንታት ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ ገልጸዋል። ክሱ የሚመሰረት ከሆነ ከቻትጅፒቲ አንጻር የቀረበ የመጀመሪያው ክስ ይሆናል ተብሏል።

3. ትዊተር ቀደም ባሉት ጊዜያት በነጻ ሰማያዊ ባጅ የወሰዱ አካውንቶች ወደ ክፍያ ስርዐት የማይገቡ ከሆነ አገልግሎቱን እንደሚያቋርጥ አስታውቋል። ይህ የተገለጸው የትዊተር ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢሉን መስክ በሳምንቱ መጀመሪያ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ረዘም ያለ ቆይታ ነው። መስክ አገልግሎቱ የሚቋረጠው ቀንም እአአ ሚያዚያ 20፣ 2023 መሆኑን በትዊተር ገጹ አስነብቧል። የቆዩ ሰማያዊ ባጆች (Legacy Blue Checks) ለልሂቃን ብቻ መታደላቸውን ለቢቢሲ የገለጸው መስክ ይህም የተወሰኑ ሰዎች ሀሳብ በተለየ ሁኔታ እንዲስተጋባ ያደረገ አሰራር ነበር ብሏል። የክፍያ ስርዐቱ ለሁሉም የአካውንት ባለቤቶች እኩልነትን እንደሚያጎናጽፍ አስረድቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መስክ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ “በቀጣይ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰማያዊው የትዊተር ባጅ የሚጠፋ መሆኑንም ተናግሯል” በማለት አሳሳች መረጃ ማሰራጨቱን ተመልክተናል።

✅️ በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌግራም ሊንኮቻቸው:

– በሰኞ መልዕክታችን ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመለየት የሚረዱ ነጥቦችን በትግረኛ አቅርበናል፡ https://t.me/ethiopiacheck/1958

– የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ እንደታሰሩ የተሰራጨን መረጃም አጣርተናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1959

– እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዝደንት ሰጡት ተብሎ የተሰራጨ መግለጫን ፈትሸናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1960

– በደብረ ብርሃን ከተማ ውሃ ተበክሏል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ “ሀሰት” ነው በማለት የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ያስታወቀበትን መረጃ አጋርተናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1961

-ኢትዮ 360 ሚዲያ ከአውድ ውጭ ያጋራውን ፎቶም አጋልጠናል:
https://t.me/ethiopiacheck/1962

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::