ቻትጂፒቲ (ChatGpt ) እያመጣቸው የሚገኙ ጥቅሞች እና ስጋቶች

የካቲት 9፣2015 ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቢያንስ የተወሰነ ጊዜ የሚያሳልፉ ወይም የቴክኖሎጂ ዜናዎችን የሚከታተሉ ከሆነ ስለ ‘ቻትጂፒቲ’ (ChatGpt ) ሰምተው ይሆናል።

እጅግ ያማረ እና ቀላል ነው፣ በፈለጉት ሰአት ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ጠይቀውት መልስ የለኝም አይልም፣ ያዋራዎታል።

የኦፒያን አናላይቲክስ መስራች የሆነው ዘላለም ግዛቸው በቀላሉ ለመረዳት ከፈለጋቹ እንደ ሮቦት አስቡት ይለናል።

“በማንኛውም ቋንቋ እ.አ.አ እስከ 2021 ድረስ ያሉ የሰው ልጅ ለአመታት ያከማቻቸውን መረጃዎች ይዞ እጅግ ሰፊ በሆነ እውቀት የሰለጠነ የቴክኖሎጂ መሳሪያ ነው” ሲል ያስረዳል።

ለምሳሌ እስከ አሁን የተለያየ የመረጃ ክምችት ያላቸውን ጉግል እና ቢንግን ስንጠቀም ኖረዋል። ስለ አንድ ጉዳይ የተጠየቀው የጉግል ስልተ-ቀመር ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮችን ፈልጎ ይሰጠናል።

ይህ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ከኢንተርኔት፣ መጻሕፍ፣ መጽሔቶች እና የዊኪፒዲያ መረጃዎች በማሰባሰብ የሰለጠነ ሲሆን በአጠቃላይ 300 ቢሊዮን ቃላቶች ስርአቱ ውስጥ ተካተዋል።

ባለፈው ህዳር ወር ይፋ የሆነው ቻትጂፒቲ (Chat generative pre-trained transformer) ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ማንኛውንም አይነት ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ መረጃ ማግኘት፣ የቢዝነስ ፕሮፖዛል ወይም ምግብ ማዘጋጀት ቢፈልጉ በሰከንዶች ውስጥ ሰርቶ የሚሰጥ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ መሳሪያ ነው።

ቻትጂፒቲን በብዛት እንደሚጠቀም የሚናገረው የቴክኖሎጂ ባለሙያው ዘላለም “ለእኔ ስራዬን አቅሎልኛል፤ በቻትጂፒቲ የማልሰራው ስራ የለም” ሲል ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግሯል።

Open AI የሚያስተዳድረው ከዚህ ቀደም የነበረው ‘InstructGPT’ ጎጂ እና አታላይ ምላሾች የሆኑ መልሶች ያሾልክ ነበር።

አሁን የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻለውን አዲሱ ቻትጂፒቲ ደግሞ ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት ይሆናል የሚሉ የቴክኖሎጂ ተንታኞች አሉ።

ከሁሉም ይልቅ ግን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት የሃሰት መረጃን ለማሰራጨት አቅም ይኖረዋል የሚል ስጋት በርካቶች ያነሳሉ።

ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ለስርአቱ የምንጠይቀው መረጃ መልሱን እስላወቅን ድረስ በስህተት የሚሰጠን መልስ ስህተቱ የት ድረስ እንደሆነ ማወቅ አንችልም የሚለው ነው።

ይህ ማለት ቴክኖሎጂው እ.ኤ.አ እስከ 2021 በበይነ መረብ ያሉ መረጃዎችን የያዘ ሲሆን አንድም ራሱን አዲስ መረጃ የማይማር መሆኑ እና የኢንተርኔት መረቡ በተሳሳተ መረጃ የተሞላ መሆኑ ስጋትን ይፈጥራል።

ኦፕን ኤአይ ኩባኒያ ከወራት በፊት ‘ChatGPT’ን ይፋ ሲያደርግ ችግር ያለባቸው መልሶችን ሊያመጣ እና የተዛባ ባህሪን ሊያሳይ እንደሚችል ጠቁሟል። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ አሳማኝ የሆኑ ግን የተሳሳቱ ወይም ትርጉም የለሽ መልሶች ይጽፋል ሲል ያስጠነቅቃል። በመሆኑም በቀጣይነት ይህን ስርዓት ለማሻሻል ደግሞ የተጠቃሚ ግብረመልስ ለመሰብሰብ ክፍት መሆኑን ይገልፃል።

ተጨማሪ ጥናት ቢያስፈልገውም መረጃን በማጣራት ስራዎች ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል የሚለው የቴክኖሎጂ ባለሙያው ዘላለም “አንደኛ ፈጣን እና የሰለጠነ ሮቦት ነው፤ አንድ ሰው በሚፈልገው መንገድ ደግሞ መረጃ ያቀርባል። ስለዚህ አንዳንዴ ለተሳሳተ መረጃ ሊውሉ የሚችሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፤ የፈለግከውን ነገር ለማድረግ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ስለዚህ ለሐሰት መረጃ ልትጠቀምበት የማይትችልበት ምንም መንገድ የለም” ብሎ ያብራራል።

የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አብዛኛው ጊዜ ኩባኒያዎች የመሰል ቴክኖሎጂዎች እጣ ፈንታ እንደማይቆጣጠሩ በመግለጽ ያስጠነቅቃሉ።

እንደ ChatGPT፣ LaMDA እና Galactica ያሉ ስርዓቶች ደግሞ በነጻነት ለዓመታት በተሰራጩ ሃሳቦች፣ የምርምር ወረቀቶች እና የኮምፒውተር ኮድ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ይላሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::