በረሽድ አብዲ የተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ

misleading information shared by Rashid Abdi

መጋቢት 30፣ 2015

በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት በመስጠት የሚታወቀው ረሽድ አብዲ ከ351 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የትዊተት አካውንቱ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ልዩ ሀይሎችን ማፍረስ ህገ-መንግታዊ አይደለም ብለዋል የሚል መረጃ ማጋራቱን አይተናል።

ረሽድ የጄኔራሉ አስተያየትም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቋም ጋር የሚጣረስ መሆኑን አክሏል።

ረሽድ አብዲ ያጋራው መረጃ የተሳሳተ ሲሆን ጄኔራል አበባው ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ-ምልልሳቸው ላይ የልዩ ሀይሎች አደረጃጀት ህገ-መንግስታዊ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ጄኔራሉ በዚሁ ቃለምልልስ ልዩ ሀይሎች “ከሀገሪቱ ህገ-መንግሥት አንፃር ሲታይ አወቃቀራቸው ህጋዊ አይደለም፤ ህገመንግሥቱም እውቅና አይሰጣቸውም” ብለዋል።

የተሳሳተውን መረጃ ያሰራጨው ረሽድ ከሰዐታት በኃላ ‘ግልጽ ለማድረግ’  በሚል በአዲስ የትዊተር ትሬድ (twitter thread) መልዕክት ያጋራ ሲሆን ጄኔራሉ የሰጡት አስተያየት ከኦፊሴላዊው የመንግስት አቋም የሚጣረስ አለመሆኑን ከአንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን መስማቱን አስፍሯል። ነገር ግን ከቀድም ሲል ያጋራውን የተሳሳተ መረጃ አላጠፋም።

ረሽድ አብዲ መቀመጫውን ናይሮቢ፣ ኬንያ በማድረግ በተለይም በኢትዮጵያና በሱማሌያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች እንዲሁም ሰሃን ሪሰርች የተባለ ተቋም በሚያሰራጫቸው በራሪ ወረቀቶች (news letters) ምልከታውን በማጋራት ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::