ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል ማን ምን ሊሰራ ይገባል?

Disinformation undermines citizens ability to make informed decisions

መጋቢት 2፣ 2015 ዓ.ም

ሀሰተኛ መረጃ ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን የመወሰን አቅማቸውን በማቀጨጭ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን ያዛባል፤ በአካባቢያዊ እና ሀገር አቀፍ ምርጫዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል እንዲሁም በማህበረሰቦች መካከል መከፋፈልን እና መካረርን በማስፋት ለግጭት በር ይከፍታል።

በዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እና በማህበረሰቦች መስተጋብር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት እንደ ኢትዮዽያ ቼክ የመሳሰሉ የመረጃ አጣሪዎች (fact-checkers) ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም ችግሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የሲቪክ ድርጅቶች፣ የማህበረሰብ ትስስር መድረኮች እና መንግስት ተቀናጅተው የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል።

ዜጎች ስለሚዲያ እና ስለመረጃ ያላቸውን ንቃት እና ግንዛቤ ማሳደግ (media and information literacy) ሀሠተኛ መረጃ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመግታት አይነተኛ መፍትሄ ነው። ንቃት እና ግንዛቤ ያላቸው ዜጎች ትክክለኛ መረጃ ከየት ማግኘት እንዳለባቸው ያውቃሉ።

ለሀሠተኛ መረጃ ያላቸውን ተጋላጭነት ይቀንሳሉ። ይህም በእውቀት ላይ የተመሰረት ውሳኔ እንዲወስኑ ያስችላቸዋል። በዚህ ረገድ የሲቪክ ድርጅቶች ጉልህ ሚና መጫዎት ይችላሉ።

የሲቪክ ድርጅቶች የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እና ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ዜጎችን የማንቃት እና የማስተማር ስራ መከወን እንዲሁም ሀሠተኛ መረጃን የተመለከቱ ይዘቶች በስርዐተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ግፊት በማድረግ፣ የነቃና ግንዛቤ ያለው ትውልድ እንዲፈጥር የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ፊንላንድ እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ ሀሠተኛ መረጃን የተመለከቱ ይዘቶችን በስርዐተ-ትምህርቷ በማካተት እና የተቀናጀ የንቃትና የግንዛቤ ዘመቻዎችን በማካሄዷ፣ የሀሠተኛ መረጃ ተጽዕኖን መቋቋም ረገድ በብዙዎች በምሳሌነት ትጠቀሳለች።

በሌላ በኩል እንደ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ቴሌግራም እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማህበራዊ ትስስር መድረኮች የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ይታወቃል።

በኢትዮዽያ ህግም ያስገድዳቸዋል። እነዚህን መድረኮች ትክክለኛ መረጃ የሚያሰራጩ ገጾችና ቻነሎች በቅድሚያ የመታየት ዕድል እንዲያገኙ በማስቻል፤ ዜጎች ሀሠተኛ መረጃን ሪፖርት የሚያደርጉበትን አካሄድ ቀላል እና በሚረዱት ቋንቋ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም ሪፖርቶችን እና ይዘቶችን የሚከታተሉ በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ የሀሠተኛ መረጃ ስርጭት እንዲቀንስ ሀላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

በተመሳሳይ ሚዲያዎች በተቋማቸው ውስጥ መረጃ የሚያጣራ ክፍል በማቋቋም እና ጋዜጠኞቻቸው ስለ መረጃ ማጣራት ሂደት በቂ እውቀት እንዲኖራቸው በማሰልጠን ሀሠተኛ መረጃ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን መወጣት ይችላሉ።

መንግስት የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የወጣውን ህግ በአግባቡ እንዲፈጸም የማድረግ ሀላፊነት ያለበት ሲሆን፣ ከሲቪክ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዜግች ስለ ሚዲያ እና መረጃ በቂ ንቃትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማገዝ ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም የማህበራዊ ትስስር መድረኮች የሀገሪቱን ህግ ስለማክበራቸው መቆጣጠር ይገባዋል። የመረጃ አጣሪዎች፣ የሲቪክ ድርጅቶች፣ የማህበራዊ ትስስር መድረኮች እና መንግስት የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ሀላፊነታቸው ከተወጡ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ዜጎችም ስለ ሚዲያ እና መረጃ ያለቸውን ግንዛቤ በማሳደግ እንዲሁም ህግ በማክበር የራሳቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::