ኢንተርኔትንና ተያያዥ የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ከሰሞኑ የታየ ለየት ያለ የማጭበርበር ድርጊት

A unique act of fraud that has been seen recently using the Internet and related digital communication methods

የካቲት 29፣ 2015 ዓ.ም

ኢንተርኔትንና ተያያዥ የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አይነተ-ብዙ የማጭበርበር ድርጊቶች ይፈጸማሉ።

ኢትዮጵያ ቼክም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሚዲያ ቅኝትና ክትትል በማድረግ እንዲሁም ከተከታታዮቹ የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶችን ሲያጣራና ሲያጋልጥ ቆይቷል።

ከነዚህም መካከል እንደ ኢሉሚናቲ፣ 666 ፣ ሉሲፈር ወዘተ ያሉ አምልኮዎችን (cults) በመቀላቀል በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ያግኙ የሚሉት በጣም የተለመዱ ናቸው።

ከሰሞኑም በኢትዮጵያ ህጋዊ እውቅና እንዳለው የሚገልጽና በአባልነት ለሚቀላቀሉ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞች እንደሚያስገኝ የሚያስተዋውቅ ጽሁፍ በፌስቡክና በቴሌግራም ሲዘዋወር ተመልክተናል።

ማስታወቂያው የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም በተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶች የሚጋራ ሲሆን አባል ለመሆን መታወቂያ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት፣ ጉርድ ፎቶና ቅድመ ክፍያ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።

ይህን ለመፈጸምም በ0989266370 የስልክ ቁጥር እንዲደውሉ ይጋብዛል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከላይ የተጠቀሰውን የስልክ ቁጥር እና በስልክ ቁጥሩ የተከፈተ የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም ማጣራት አድርጓል።

ማስታወቂያውን የሚያጋሩ ሰዎች ህጋዊ እውቅና አለን ቢሉም እውቅናቸው ለማሳየት ፍቃደኛ አልሆኑም። በተጨማሪም ከስልክ ቁጥሩና በስልክ ቁጥሩ ከተከፈተ የቴሌግራም ቻናል ውጭ በአካል ለመገኘትም ሆነ አድራሻቸውን ለመግለጽ አልፈቀዱም። ይልቁንም ቅድመ ክፍያ ብሩንና ዶክመንቶቹን መላክን እንደ ቅድመ ሁኔታ ይጠቅሳሉ።

በተጨማሪም በሚያጋሯቸው ይዘቶች ላይ ባደረግነው ማጣራት የተለመዱ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ አስተውለናል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ዳሰሳ ይህን የመሰሉ በርካታ ማስታወቂያዎች በተለያዩ ስሞችና ስልክ ቁጥሮች በተለይም በፌስቡክ ግሩፖች በስፋት እንደሚጋሩ ተመልክቷል።

የሚዲያ አጠቃቀም ንቃታችንን ከፍ በማድረግ ይህን ከመሰሉ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች እራሳችንን እንጠብቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::