በጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ፌስቡክ ላይ የቀረበ አሳሳች መረጃ

girum challa

መጋቢት 12፣ 2015 ዓ.ም

ጋዜጠኛ ግሩም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ሀብታም በመሆን 6ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በምስል የተደገፈ አንድ መረጃ በትናንትናው እለት አጋርቶ ነበር። በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያሰፈረው ፅሁፍ “ETHIOPIA IS THE 6TH RICHEST COUNTRY IN AFRICA” ይላል።

ጋዜጠኛው ባጋራው ምስል ላይ ናይጄርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ አልጄርያ፣ ሞሮኮ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት እና ታንዛንያ ከ1- 10 ያለ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ይታያል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ መረጃ ዙርያ ዳሰሳ አድርጓል።

በመጀመርያ መመልከት የቻልነው ጋዜጠኛው ያጋራው የኢትዮጵያን ጥቅል ምርት (Gross Domestic Product/GDP) የሚያሳየውን የአለም ባንክ የ2021 መረጃ ነው። ይህ መረጃ በዚህ ሊንክ ይገኛል: https://data.worldbank.org/indicator/NY.GDP.PCAP.CD

ጥቅል ምርት (GDP) በአንድ ሀገር ውስጥ የተመረቱ ቁሶች እና የተሰጡ አገልግሎቶች ጥቅል የገንዘብ መጠን (monetary value) ሲሆን የሀገራትን የኢኮኖሚ መጠን ለመለካት እንጂ የሀብት መጠን ለማወቅ እንደማያስችል ይታወቃል።

የኢትዮጵያ GDP 111 ቢልዮን ዶላር፣ የኬንያ ደግሞ 110 ቢልዮን ዶላር ነው

በኩዌት የኢኮኖሚክስ ሳይንስ ጥናት ማዕከል (KISR) ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር አየለ ገላን ሀገራትን በGDP ማነፃፀር አሳሳች ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ።

አቶ አየለ ይህንን ሲያስረዱም: “ለምሳሌ የኬንያን የነፍስ ወከፍ ገቢ ( GDP per capita) እናስላ። ኢትዮጵያ ከኬንያ ከእጥፍ የሚበልጥ የህዝብ ቁጥር አላት። የGDP መጠኑን በህዝብ ቁጥር ስናካፍለው የኢትዮጵያ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 927 ዶላር እንዲሁም የኬንያ 1,903 ዶላር ይሆናል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዜጎች የነፍስ ወከፍ አመታዊ ገቢ ከኬንያውያን ያንሳል፣ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ከኬንያውያን ከግማሽ ያነሰ ገቢ አላቸው።”

አክለውም “በኬንያ ያሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተማሪዎች ኢትዮጵያ ካሉ አቻዎቻቸው 700 ፐርሰንት ከፍ ያለ ክፍያ ያገኛሉ፣ በናይሮቢ ያለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ክፍያ ደግሞ በአዲስ አበባ ካለው በ1,300 ፐርሰንት ይበልጣል። ይህ እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ያለው የኑሮ ውድነት ከኬንያ ይበልጣል።”

እነዚህ ነጥቦች እንደሚያሳዩት በጋዜጠኛው የተጋራው መረጃ አሳሳች ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::