“እኛ እንዲህ አይነት መረጃ አላወጣንም”— የህንዱ ኦፕን መፅሄት አርታኢ ለኢትዮጵያ ቼክ

False report by EBC claiming that pm Abiy Ahmed is selected by India’s Open Magazine as one of Africa’s democratic leaders

የካቲት 18፣2015

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ለውጦችን ማምጣት የቻሉ ዲሞክራቲክ መሪ ናቸው ሲል ኦፕን መፅሄት ገልጿል” የሚል ዜናን ኢቢሲ ከትናንት ምሽት ጀምሮ እስከዛሬ ቀትር ሰዓት ድረስ ሲዘግብ ነበር።

ኢቢሲ በተለይ በትናንት ምሽት ዘገባው በህንድ የሚታተመው ‘ኦፕን ማጋዚን’ በአፍሪካ የዲሞክራሲያዊ መሪዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል ብሎ ይጠቅስና “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በ1ኛ ደረጃ ላይ አስቀመጠ” የሚል መረጃ አጋርቷል።

“መጽሔቱ በአፍሪካ በቅርብ ዓመታት ወደ ስልጣን የመጡ ዲሞክራሲያዊ መሪዎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀዳሚነት የተቀመጡ ሲሆን፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የዚምባብዌው ኢመርሰን ምናንጋግዋ እና የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል” ይላል ዘገባው።

ኢትዮጵያ ቼክ ከተከታዮቹ የደረሱትን የማጣራት ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ለመፅሄቱ አርታኢ (ኤዲተር) ኤስ ፕራሳናራጃንን በኢሜይል ጥያቄ አቅርቧል።

አርታኢው “እኛ እንዲህ አይነት መረጃ አላወጣንም፣ የእኛም ዘገባ አይደለም። ይህንን ልናረጋግጥላችሁ እንችላለን” የሚል ምላሽ ለኢትዮጵያ ቼክ ማምሻውን ልኳል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዲጂታል መልኩ የታተሙ የመፅሄቱን የቅርብ ግዜ ህትመቶች የተመለከተ ሲሆን በኢቢሲ የተጠቀሰው አይነት መረጃ ይዘው እንዳልወጡ ማየት ተችሏል።

በመጨረሻም፣ የዚህ ሀሰተኛ መረጃ መነሻ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ አለሙ ስሜ ስም ተመሳስሎ በተከፈተ ሀሰተኛ የትዊተር አካውንት ቀድሞ የተሰራጨ ተመሳሳይ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ማየት ይቻላል። ይህ አካውንት ሀሰተኛ እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ በተከታታይ መረጃዎችን አቅርቦ ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::