በአፋር ህዝቦች ፓርቲ የፌስቡክ ገፅ ላይ የተሰራጨ ሀሰተኛ መረጃ

false information shared by Afar People's Party

መጋቢት 27፣ 2015

የአፋር ህዝቦች ፓርቲ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገፁ ላይ ከስድስት ቀናት በፊት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም በአየርላንድ “Distant Lord Mayor of Belfast” የሚባል ሽልማት እንደተቀበሉ ከአንድ ምስል ጋር መረጃ አጋርቶ ነበር።

መረጃው አክሎ ይህ ሽልማት “ለጥቁር ሰው” ሲበረከት ሁለተኛው ብቻ መሆኑን ጠቅሶ ሽልማቱ “ከሰሜን አየርላንድ ብሄራዊ ጀግና” የሚስተካከል መሆኑን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ማጣራት ያደረገ ሲሆን መረጃው የተሳሳተ መሆኑን ደርሶበታል።

ፎቶው መቼ እና የት ተወሰደ?

ይህ ምስል/ፎቶ የተወሰደበት ፕሮግራም ሰሜን አየርላንዶች የፖለቲካ አመለካከታቸውን ከሃይማኖታቸው ጋር በማቀላቀላቸው ከደረሰባቸው ማኅበረሰባዊ ውድመት ለማገገም እንዲሁም የፖለቲካ ልዩነታቸውን ለመፍታት የሄዱበትን ርቀት ለመማር 11 ያህል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በሰሜን አየርላንድ ዋና ከተማ ቤልፋስት ለአንድ ሳምንት ያህል (ከመጋቢት 17 እስከ መጋቢት 23) በቆዩበት ወቅት የተወሰደ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

አቶ አደም የተነሱት ፎቶ ምን ያሳያል?

በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መሀል አንዱ የነበሩት የአፋር ህዝቦች ፓርቲ መሪ አቶ አደም ሙሳ የ “Lord Mayor of Belfast” ኒሻን ታሪክ ገለፃ በተደረገበት ወቅት ፎቶ ለመነሳት ጥያቄ አቅርበው እንደተፈቀደላቸው ሌላኛው በስፍራው የነበሩ አንድ አመራር ለኢትዮጵያ ቼክ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ኒሻን አመጣጥ እና አለባበስ ዙርያ መረጃዎችን የተመለከተ ሲሆን ይህ ሽልማት ለአቶ ሙሳ እንደተሰጠ የሚገልፅ መረጃ እንደሌለ ተመልክተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::