“በ8100 A አማካኝነት የሚደረጉ ድጋፎች የዕጣ ሽልማት የሚያስገኙ አይደሉም” የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት

የካቲት 15፣2015

“በ8100 A አማካኝነት የሚደረጉ ድጋፎች የዕጣ ሽልማት የሚያስገኙ አይደሉም”— የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ቼክ

“ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆን በተከፈው የአጭር መልዕክት ቁጥር 8100 A ላይ በየቀኑ አንድ አንድ ብር ስናዋጣ ቆይተናል። በዚህም የሎተሪ ቁጥር በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ሲደርሰን ቆይቷል። የሎተሪ እጣ ግን ሲወጣ አይተን አናውቅም። እባካችሁ አጣሩልን” የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች ደርሶናል።

ጉዳዩን በተመለከተ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ማብራሪያ ጠይቀናል።

“በ 8100 A አማካኝነት የሚደረጉ ድጋፎች የዕጣ ሽልማት የሚያስገኙ አይደሉም፤ ዜጎች ለግድቡ በፍቃደኝነት የሚያደርጉት አስተዋጾ ነው” በማለት የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ሀይሉ አብረሃም ምላሽ ሰጥተዋል።

የ “8100 A” ገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በ2012 ዓ.ም መጀመሩን የገለጹት አቶ ሀይሉ በወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ ስለነበር ከንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ዜጎች አስተዋጾ እንዲያደረጉ በማሰብ መሆኑንም አብራርተዋል። “ይህም ምንም አይነት ሽልማት የሚያስገኝ አይደለም” ሲሉ አክለዋል።

ሆኖም በ2007 እና በ2008 ዓም ሽልማት የሚያስገኝ የ8100 ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደነበር ነገርግን መቋረጡን ዳሬክተሩ አስታውሰዋል። “ጥያቄውን ያነሱ ሰዎች ምናልባት ሁለቱ መርሃ ግብሮች ተመሳሳይ መስለዋቸው ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል።

በ2012 ዓ.ም በተጀመረው የ8100 A መርሃ ግብር 46 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ንቁ ተሳታፊ እንደሆኑ እንደሚገመትም ዳሬክተሩ ተናግረዋል። በዚህም በየወሩ በአማካኝ 12 ሚሊዮን ብር እየተሰበሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለተሳታፊዎች በየቀኑ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች እንደሚላኩ የገለጹት አቶ ሀይሉ ይህ ማለት ግን መልዕክት በተላከ ቁጥር ብር እየተቆረጠባቸው ነው ወይም የሎተሪ እጣ ቁጥር እየተላከላቸው ነው ማለት አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ዜጎች በ8100 A ላይ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::