በመገንባት ላይ ያለውን አዲሱ የአባይ ድልድይ ያሳያል ተብሎ ትዊተር ላይ የተሰራጨ የተሳሳተ ምስል

False image of a bridge under construction in Bahir Dar

ግንቦት 09፣ 2015 ዓ.ም

ከ3,790 በላይ ተከታይ ያለውና ‘ CHERBOLE’ የሚል መጠሪያ የሚጠቀም የትዊተር አካውንት በባህርዳር በመገንባት ላይ ያለውን አዲሱን የአባይ ድልድይ ያሳያል ያለውን ፎቶ ማጋራቱን ተመልክተናል።

ፎቶው ላይ ለአገልግሎት ክፍት የሆነ ግዙፍ ድልድይና ባለብዙ መስመር ፈጣና መንገድ እንደሚታይ አስተውለናል።

ምንም እንኳን በባህርዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ ድልድይ እየተገነባ መሆኑ እውነት ቢሆንም ከላይ የተጠቀሰው አካውንት ያጋራው ፎቶ ከሌላ ቦታ የተወሰደ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

ፎቶው በቻይና የሚገኝውን የሄሂ ድልድይን (Haihe Bridge) የሚያሳይ ሲሆን ፎቶው እአአ መስከረም 30/2021 ዓ.ም ኢኮኖሚክ ዴይሊ ቻይና Economic Daily, Chaina) በተባለ የትዊተር አካውንት የተጋራ ነበር።

የባህርዳሩ የአባይ ድልድይ በግንባታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመጭው ሰኔ እንደሚጠናቀቅ በትናትናው ዕለት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የስራ ሂደቱን በጎበኙበት ወቅት መገለጹን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

መስከረም 8/2012 ዓ.ም የተጀመረውን የዚህን ድልድይ ግንባታ የቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በተቋራጭነት እንዲሁም የቱሩኩ ቦቴክ ቦስፈረስ እና አገር በቀሉ ስታዲያ ኢንጅነሪንግ በአማካሪነትና በንዑስ አማካሪነት እያከናወኑት መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የግንባታ ወጭውም 1.437 ቢሊዮን ብር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር ስፋት አለው። የድልድዩ አይነትም ኤክስትራዶስድ (Extradosed) የሚባለው መሆኑን ተገልጿል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::