“ይሄ 100 ፐርሰንት ግልጽ ዉሸት ነው። አሻሚ የሆነ ነገርም አይደለም”— የአፋር ክልላዊ መንግስት ለኢትዮጵያ ቼክ

afar

መጋቢት 12፣ 2015 ዓ.ም

‘ABYSSINIA’ የሚል ስም ያለዉ እና ከ7,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካዉንት “ወደ ትግራይ ሊገባ የነበረ ከባድ መሳሪያ አፋር ላይ ተይዟል” በሚል ይህን ምስል አጋርቷል።

ምስሉ በርከት ያሉ ከባድ መኪኖች ላይ የተጫኑ የጦር መሳሪያዎችን የሚያሳይ ሲሆን አካዉንቱ መረጃዉን ያጋራዉ ትላንት ጥር 11/2015 ነው።

ይህን መረጃ ከ50 በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎች መልሰዉ ያጋሩት (retweet ያረጉት) ሲሆን ከ120 በላይ መዉደድ (like) አግኝቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ስለ መረጃዉ የአፋር ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ አህመድ ከሎይታን ያናገር ሲሆን እርሳቸዉም “ይሄ 100 ፐርሰንት ግልጽ ዉሸት ነው። አሻሚ የሆነ ነገርም አይደለም” ብለዋል።

አቶ አህመድ ምስሉ በሁለተኛ ዙር ከትግራይ ወደ መሃል ሀገር በመከላከያ እየተጓጓዙ ያሉ የጦር መሳሪያዎችን የሚያሳይ መሆኑን ነግረዉናል።

“ይሄ ግልጽ የሆነ ነገር ነዉ። በትግራይ የነበረ፤ ለመከላከያ ያስረከቡት እና ሀገር መከላከያ ሰራዊት እያጓጓዘዉ ያለ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ልይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሎቹ ከቀናት በፊት በርከት ባሉ የፌስቡክ እና ትዊተር ተጠቃሚዎች ሲጋሩ የነበሩ መሆናቸዉን ተመልክቷል።

በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎችም በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና ህወሐት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመዉ ስምምነት መሰረት ህወሐት እጅ የነበሩና መከላከያ ሰራዊት ተረከቧቸዉ ከትግራይ ወደ መሀል ሀገር በመጓጓዝ ላይ ያሉ የጦር መሳርያዎች መሆናቸዉን በመግለጽ ምስሎቹን ሲያጋሩ እንደነበር ተመልክተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::