የስኳር በሽታን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ‘በሰአታት ውስጥ ማጥፋት ተችሏል’ በሚል እየተሰራጨ የሚገኘው መረጃ አሳሳች መሆኑን የጤና ባለሞያዎች አስጠነቀቁ!

ኀዳር 5፣ 2017
“በሦስት ሰአታት ውስጥ የስኳር ህመምን ከነዘርማንዘሩ ማጥፋት ተችሏል” የሚል መረጃ በቲክቶክና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።
እነዚህ ‘ET Smart Care’ በሚል የቲክቶክ አካውንት እየተሰራጩ የሚገኙ የህክምና መረጃዎች “የክሩስፐር ጂን ኤዲቲንግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሦስት ሰአት ውስጥ የስኳር ህመምን ከነዘር ማንዘራቸው ማጥፋት ተችሏል። እውነት ነው ከነዘር ማንዘራቸው ማጥፋት ችሏል” ሲል ይደመጣል።
መረጃዎቹን እያሰራጨ የሚገኘው ግለሰብ ‘አካውንቲንግና ህግ’ ጨምሮ የተለያዩ የህክምና ክህሎቶች እንዳሉት የሚገልጽ ሲሆን ‘የክሩስፐር ጂን ኤዲቲንግ’ ቴክኖሎጂ በአሜሪካና ቻይና ውጤታማ መሆኑን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ የስኳር ህመም ህክምና እየተሰጠ እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ማጋራቱን ኢትዮጵያ ቼክ መገንዘብ ችሏል።
እነዚህ መረጃዎች የስኳር ህመም ያለባቸው ቤተሰቦች ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጨምሮ ሌሎች የህክምና ተቋማት ጋር በመሄድ ይሄንን “ፈዋሽ ህክምና” እንዲታዘዝላቸው አልያም ወደ ውጭ አገራት ሪፈር እንዲባሉ ለመጠየቅ ሆስፒታሎችን እያጨናነቁ እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ከህክምና ባለሞያዎች ያገኘው መረጃ ያመላክታል።
ይህ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ የሚገኘው መረጃ አሳሳችና ቴክኖሎጂው በስኳር ህመም ህክምና አገልግሎት ላይ ያልዋለ እንደሆነ በመግለጽ መረጃው የስኳር ህመምተኞች፣ ቤተሰቦችና የጤና ባለሞያዎች እያሳሳተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የስኳር በሽታ ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር መላኩ ታዬ በአሁኑ ወቅት የስኳር ህመም የሚያጠፋ ህክምና እንደሌለ በመግለጽ ‘ክሩስፐር ጂን ኤዲቲንግ’ “በምርምር ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።
ለህክምና ከመፈቀዱ በፊት ብዙ ተጨማሪ ጥብቅ ምርምርና ጥናቶች ያስፈልጉታል” ሲሉ ለመረጃ ማጣርያ ዴስካችን አረጋግጠዋል።
አይነት አንድ የስኳር ህመም በዘላቂነት በኢንሱሊን መድሃኒት መታከም እንዳለበት የህክምና ባለሞያዎች ያስገነዝባሉ። አይነት ሁለት የስኳር ህመም ደግሞ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች (በአመጋገብ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ክብደትን በመቆጣጠር) በማድረግ እንዲሁም የደም ስኳር መጠንን ለመቆጣጠር የሚረዱ የተለያዩ መድሃኒቶች በመውሰድ መቆጣጠር ይቻላል።
ከዚህ ባሻገር በሽታውን ለማከም የሚረዱ የስቲም ሴል ምርምር ጨምሮ የተለያዩ የሙከራ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በመሆኑም የህክምና ሳይንስ ተስፋ ሰጭ ህክምናዎች በንቃት እየመረመረ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር መላኩ ሳይንቲስቶች ከኢንሱሊን ባለፈ ለስኳር ህመም መፍትሄ ለማግኘት እየተደረጉ ያሉት የሙከራ ደረጃ ህክምናዎች ገና ጥቅም ላይ ለመዋል ዝግጁ አለመሆናቸው ግን አስገንዝበዋል።
ከዚህ ውጭ የስኳር ህመም በሌላ ቴክኖሎጂ ይድናል በሚል አሳሳች መረጃ ምክንያት በሽተኞች በህክምና የሚሰጣቸው ኢንሱሊን እንዳያቆሙ ባለሞያው አስገንዝበዋል።
“ኢንሱሊን ለአይነት አንድ የስኳር ሕክምና የማዕዘን ድንጋይ ነው፤ ኢሱሊን እንደ ውሃና ኦክስጅን ለሜታቦሊዝም መሳለጥ፣ ለጤናማ እእድገትና ሰውነት ግንባታ አስፈላጊ የሆነ ሆርሞን ነው። ስለሆነም ይህ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ኢንሱሊንን በተፈጥሮ ማመንጨት ስማይችሉ መደበኛ የኢንሱሊን መርፌ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። የኢንሱሊን ሕክምናን ማቆም በጥቂት ቀናት ውስጥ ለህይወት አስጊ ይሆናል” ሲሉ ‘የአይነት አንድ ስኳር ህክምና አሁናዊ መመሪያዎችና ተስፋ ሰጪ ምርምር ውጤቶች’ በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጽሑፍ ጠቅሰዋል።
‘ክሪስፐር/ካስ9 የጂን ኤዲቲንግ’ ምንድን ነው?
የዘረመል እርማት ማድረግ ህክምና በጣም የተራቀቀ ሲሆን ለበሽታ የሚያጋልጠውን ዘረመል ነጥሎ የሚሰረዝበት፣ የሚሻሻልበት ወይም የሚተካበት የጄኔቲክ ሳይንስ ነው።
ይህም ችግር ያለበትን ዘረመል ለይቶ በማረም ማስተካከልን ያካትታል። ይህን የህክምና ዘዴ የሚሰራበት ቴክኖሎጂ ክሪስፐር ጂን አርትዖት (CRISPR Gene Editing) ይባላል።
በታኅሣሥ 8፣ 2023 የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ይሄንን ቴክኖሎጂ በቀይ ደም ህዋሳት ውስጥ ያለውን የሂሞግሎቢን ፕሮቲን የሚጎዳ በዘር የሚተላለፍ የደም ህመም (sickle cell disease (SCD)) ለማከም ስራ ላይ እንዲውል አጽድቆታል።
“ይህ ህክምና ገና፣ ገና በጅምር ምርምር ደርጃ ላይ ያለ ነው። የእድሜ ልክ የሆነውን የስኳር ሕክምና ሊፈውስ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል። ነገር ግን እስካሁን ኢንሱሊንን ለመተካትና ከምርመር ሙከራ ደረጃ አልፈው እንደዋና ህክምና ለመጠቀም ገና ዝግጁ አይደሉም” ሲሉ ዶ/ር መላኩ በጽሑፋቸው ያስረዳሉ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጤና ምክሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን ታማኝ ባልሆኑ ምንጮች የሚሰራጩ ቁንጽል ሃሳቦች ጤናን ሊጎዱ ስለሚችሉ መረጃዎችን አምነን ከመቀበላችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
