ጎግል ሌንስ ወደ ስራ ያስገባቸው በሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) የተደገፉ የፍለጋ አገልግሎቶች
ሰኔ 18፣ 2016
ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች በስፋት ከሚሰራጩባቸው መንገዶች መካከል ከአውድ ውጭ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምስሎችና ቪዲዮዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እንዲህ ያሉትን ምስሎችንና ቪዲዮዎች ለማጣራት ብዙዎቻችን በምልሰት ምስል የሚፈልጉ (Reverse Image Search) መተግበሪያዎችን እንጠቀማለን።
ጎግል ሌንስ (Google Lens) ደግሞ በምልሰት ምስል ለመፈለግ በቀዳሚነት ከምንጠቀምባቸው መተግበሪያዎች አንዱ ነው። ሆኖም እንደሌላዎቹ መተግበሪያዎች ሁሉ ጎግል ሌንስም ተፈላጊውን የፍለጋ ውጤት በማግኘት ረገድ የራሱ ውስንነቶች እንዳሉበት ይታወቃል።
ጎግል እነዚህን ውስንነቶች በእጅጉ የሚያሻሽሉ እና በሰውሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence- AI) የሚታገዙ የፍለጋ አገልግሎቶችን በተከታታይ ወደስራ በማስገባት ላይ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የባለብዙ ትብብር ፍለጋ (Multisearch)፣ በማክበብ ፍለጋ (Circle to Search) እንዲሁም የቪዲዮ ፍለጋ (Video Search) የተሰኙት አገልግሎቶች ይገኙበታል። ለመሆኑ አገልግሎቶቹ ምን ይዘዋል?
– ባለብዙ ትብብር መፈጊያ: በጎግል ሌንስ ላይ የተጨመረው እና በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚታገዘው አገልግሎት ከዚህ ቀደም ምስል በማስገባት ብቻ በምናደርገውን ፍለጋ ላይ ጽሁፍ እንድንጨምርበት ይፈቅድልናል። ይህም ምስሉን በተመለከተ ምን ለማወቅ እንደምንፈልግ ለማብራራት ዕድል ይሰጠናል። በዚህም ከቀድሞ በተሻለ ብቃት የምንፈልገውን መረጃ በቀላሉ ማግኘት ያስችለናል። ይህንን አገልግሎት ለመጠቀም በመጀመሪያ ወደ ጎግል መፈለጊያ እናመራለን። በመቀጠል ከመፈለጊያ በስተቀኝ ጫፍ የምትገኘውን የጎግል ሌንስ ምልክት እንነካለን። ከዚያም ለመፈለግ የመረጥነውን ምስል እናስገባለን። እንዲሁም ከምስሉ ላይ ለፍለጋችን የትኩረት ቦታ ካለ ክሮፕ (crop) ማድረግ እንችላለን። ከዚያም ‘Add to your search’ የሚለውን ጽሁፍ እንጫናለን። በመጨረሻም ከምስሉ ጎን በሚገኘው ቦታ ጽሁፍ በመጨመር የፍለጋ ውጤታችንን ማየት እንችላለን።
– በማክበብ መፈለግ: ጎግል ከጀመራቸው በሰውሰራሽ አስተውሎት ከተደገፉ አዲስ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ሲሆን ይህም መተግበሪያዎችን (applications) መቀያየር ሳያስፈልገን ስለምናያቸው ምስሎችና ቪዲዮዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያስችለናል። ለምሳሌ የፌስቡክን ወይም የዩትዩብን መተግበሪያ በመጠቀም ላይ ባለንበት ጊዜ ትኩረታችንን የሳበ ምስል ወይም ቪዲዮ ቢያጋጥመን መተግበሪያ መቀየር ሳያስፈልግን ምስሉን ወይም ቪዲዮውን በማክበብ ብቻ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንችላለን ማለት ነው። ጎግል አገልግሎቱን ከሳምሰንግ ጋር በመተባበር የሰራው ሲሆን ለመጠቀምም አዲሶቹ የሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ24 ስልኮች (Samsung Galaxy S24 series) ወይም ፒክስል 8 (Pixel 8) እና ፒክስል 8 ፕሮ (Pixel 8 Pro) ሲስተም ያላቸው አንድሮድ ስልኮች ያስፈልጉናል። አገልግሎቱ ቀለል ያለ አቀራረብ ያለው ሲሆን ለመጠቀም የስልካችንን ሆም በተን (Home Button) ረዘም ላለ ጊዜ መጫን ከዚያም የምንፈልገውን ምስል ወይም ቪዲዮ ማክበብ በቂ ነው። በዚህም የሰውሰራሽ አስተውሎቱ ስለአከበብነው ምስል ወይም ቪዲዮ ተጨማሪ መረጃ ያቀርብልናል።
– በቪዲዮ መፈለግ: ሌላኛው ጎግል ወደሙከራ ያስገባው አገልግሎት የቪዲዮ ፍለጋ ነው። ይህ በሰውሰራሽ አስተውሎት ይታገዛል የተባለው አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከቪዲዮዎች ላይ በሚወሰዱ የክሪንቅጅዎች ብቻ በመታገዝ ይደረግ የነበረውን የቪዲዮ ፍለጋ በእጅጉ እንደሚያዘምነው ተነግሮለታል። አገልግሎቱን ለመጠቀም በጎግል ሌንስ ቪዲዮ መቅረጽ ወይም መጫን ከዚያም መፈለግ በቂ ይሆናል ተብሏል። ይህ አገልግሎት ለተመረጡ ተጠቃሚዎች በሙከራ ደረጃ በመሰጠት ላይ ይገኛል።
አዳዲስ ከሚወጡ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ጋር እራሳችንን ማላመድ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በቀላሉ ለመለየት ይረዳናል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::