የኢትዮጵያ ቼክ የአርብ ሳምንታዊ ዳሰሳ

Friday roundup

ጥቅምት 08 2017 ዓ.ም

  1. ፍሪደም ሀውስ የተባለው አለም አቀፍ የመብቶች ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው አስራ ሰባት የአፍሪካ አገራት ጋር መድቧታል፡፡ ‘’ፍሪደም ኦን ኔት 2024’’ የተሰኘው ይህ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከመቶ ሀያ ሰባት ነጥብ በመስጠት ምንም ነፃነት የሌለባቸው ከሚሉት ምድብ ቀላቅሏታል። ተደጋጋሚ የኢንተርኔት ገደብ ለዝቅተኛ ነጥቡ በዋና ምክንያትነት ቀርቧል።
  1. ቴሌግራም ሪፖርት በማድረጊያ መገልገያው ላይ ማሻሻያ ማድረጉን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል። በማሻሻያውም ሪፖርት የሚያደርጉ አሉታዊ ይዘቶች አይነት እንዲጨምር ሆኗል። በተጨማሪም ለሪፖርት በሚቀርቡ ምክንያቶች ላይም በዛ ያሉ አማራጮች እንዲቀርቡ ተደርገዋል። ቴሌግራም ማሻሻያው የሚቀርቡለትን ሪፖርቶች በፍጥነትና በተሻለ መረዳት ለማሳለጥ እንደሚረዳው አብራርቷል። ቴሌግራም አሉታዊ ይዘቶችን በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ ቸልታ ያበዛል የሚሉ ወቀሳዎች ሲቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል።
  1. ተመራማሪዎች ሀሠተኛ መረጃን በተሻለ ብቃት ማጣራት የሚችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ማበልጸግ መቻላቸውን በቴክኖሎጅ ዙሪያ የሚዘግበው ፕሮግራም ኢንሳይደር ድርገጽ አስነብቧል። በአሜሪካ የኖርዝ ዳኮታ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ያበለጸጉት መረጃ አጣሪ በርከት ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅዎችን በማስተሳሰር ይሰራል የተባለ ሲሆን ውስብስብ መረጃዎችን በማጣራት ለፍጹምነት የቀረበ ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል። ይህ መረጃ አጣሪ ስሜቶችን በመረዳት ረገድም ልቆ መገኘቱ ተዘግቧል።

በሳምንቱ ያቀረብናቸው መረጃዎች የቴሌግራም ሊንኮች፥

-ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከአማካሪነታቸው እንደተነሱ ተደርጎ ተቀናብሮ የተሰራጨ ምስልን አጣርተናል: https://t.me/ethiopiacheck/2478

-ቀጣናዊ መካረሮች በሚኖሩበት ጊዜ የሚሰራጩ ሀሠተኛ መረጃዎችን የተመለከተ ጽሁፍ በትግርኛ አቅርበናል: https://t.me/ethiopiacheck/2479

-“የሶማሊያ መንግስት ለአልሸባብ አንድ ሄሊኮፕተር ሙሉ መሳርያ ሰጠ” ከሚል መረጃ ጋር ተያይዞ የተጋራ ምስልን አጣርተናል: https://t.me/ethiopiacheck/2480

-ደሴ ከተማ የተደረገን የተቃውሞ ሰልፍ ያሳያል ተብሎ የተጋራ ቪዲዮንም ፈትሸናል: https://t.me/ethiopiacheck/2481

-የካናዳ መንግስት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የስራ እድል አመቻቸ በማለት ስለሚፈጸም የማጭበርበር ድርጊት ጽሁፍ አቅርበናል: https://t.me/ethiopiacheck/2483

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::