“ምንም የተቀየረ ስርዐተ-ትምህርት የለም፣ አማርኛም ከስርዐተ ትምህርቱ እንዲወጣ አልተደረገም”— ፕሮፌሠር ክንደያ ገ/ህይወት ለኢትዮጵያ ቼክ

a false claim about the removal of Amharic subject by Tigray region education bureau from the region's curriculum

ሚያዝያ 19፣ 2015

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ከክልሉ ስርዐተ ትምህርት ማስወጣቱን የሚገልጹ መረጃዎች ባለፉት ሁለት ቀናት በስፋት ሲሰራጩ ተመልክተናል። ከመረጃው ጋር የትምህርት አሰጣጥን የሚያሳይ ሰሌዳ በምስል ተያይዞ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ ቼክ የመረጃውን ትክክለኛነት በተመለከተ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይ ክላስተር አስተባባሪ የሆኑትን ፕሮፌሠር ክንደያ ገ/ህይወትን አነጋግሯል።

ፕሮፌሠር ክንደያ “ምንም የተቀየረ ስርዐተ-ትምህርት የለም፣ አማርኛም ከስርዐተ ትምህርቱ እንዲወጣ አልተደረገም” በማለት የተሰራጨው መረጃ ሀሠተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ወደኋላ መቅረታቸውን ያስረዱት ፕሮፌሠር ክንደያ ይህን ለማካካስ የተፋጠነ (accelerated) የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ለመከተል መወሰኑን አስረድተዋል።

በዚህም አንዳንድ የትምህርት አይነቶች ከክፍል ውጭ እንዲሰጡ የሚደረጉ ይሆናል ብለዋል። ከክፍል ውጭ የሚሰጡ የትምህርት አይነቶችም የስርዐተ ትምህርቱ አካል መሆናቸውን አጽኖት ሰጥተዋል።

ከመረጃው ጋር የተሰራጨው ሰሌዳም “ሆን ተብሎ ተቆርጦ የተሰራጨ” መሆኑን ገልጸዋል።

ተቆርጦ በተሰራጨው ሰሌዳ በክፍል ውስጥ የሚሰጡ የትምህርት አይነቶች ተብለው የተዘረዘሩትን ብቻ እንደሚያሳይ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::