‘ዳጉ ሚድያ’ የሚል ስያሜ ባለው የዩትዩብ ቻናል እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች

'ዳጉ ሚድያ' የሚል ስያሜ ባለው የዩትዩብ ቻናል እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች

ሐምሌ  1፣ 2016

ዩትዩብ ላይ 270 ሺህ ገደማ ተከታታይ ያለው ‘ዳጉ ሚድያ’ ትናንትናን ጨምሮ ከሰሞኑ በርካታ ሀሰተኛ እና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ሲያጋራ ተመልክተናል።

ለምሳሌ በትናንትናው እለት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ማይክ ሀመር ጎጃም እንደገቡ እና “ከዘመነ ጋር መከሩ” የሚል እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታሩ ላይ የሙስና ክስ ተመሰረተ የሚል መረጃ አሰራጭቶ ነበር።

ይህን ቪድዮ ከ32 ሺህ በላይ ሰው የተመለከተው ሲሆን በርከት ያሉ ሰዎችም አስተያየት ሲሰጡ ተመልክተናል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ ሁለቱም መረጃዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ማይክ ሀመር “ይህ የተሳሳተ መረጃ ነው፣ አሁን ያለሁት ጅቡቲ ነው፣ ወደ አዲስ አበባ የማቀናው ገና በቀጣይ ቀናት ነው” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይህንንም በጅቡቲ እያደረጉ ያሉትን ጉብኝት የሚያሳይ የሚድያ ዳደሳ በማድረግ አረጋግጠናል።

ኢትዮ ቴሌኮምንም በተመለከተ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ምንም የተመሰረተ ክስ እንደሌለ የፍርድ ቤት እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም ምንጮቻችን በማነጋገር አረጋግጠናል።

የአንባቢ፣ አድማጭ እና ተመልካች ቅልብን የሚስቡ ነገር ግን ሀሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን አምነን ባለመቀበል እና መልሶ ለሌሎች ባለማጋራት ሀላፊነታችንን እንወጣ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::