ይህ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እንደተፃፈ ተደርጎ እየተሰራጨ የሚገኝ ደብዳቤ ሀሰተኛ ነው

ነሐሴ 30፣ 2016 ዓ.ም
በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በሚደገፈው የአፍሪካ ልማት ፈንድ እና በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስቴር በቅንጅት በሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ተሳተፉ፣ የተሳተፋችሁም የላካችሁት ዶክመንት ደርሶን እየመረመርነው ነው የሚል ደብዳቤ ከአንድ የ USAID ሎጎ ካለው ፎርም ጋር በኢሜይል እና ዋትሳፕ እየተሰራጨ እንደሆነ ተመልክተናል።
“አንዳንድ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላችሁ ወደሚቀጥለው ዙር አልፋችኋል። የተያያዘውን ፎርም በሞሙላት ላኩልን” የሚለው ደብዳቤው ‘ግዌይን አልቢና’ የተባለ/ች የ USAID ፀሀፊ እንደፃፈችው ተደርጎ ቀርቧል። በዚህ ዙርያ ማንኛውም አይነት ሙስና በጥብቅ እንደሚያስቀጣም ያሳስባል።
የደብዳቤውን እና የፎርሙን እውነተኛነት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ አዲስ አበባ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ማብራርያ ጠይቋል።
ኤምባሲው በሰጠው ምላሽ በምስሉ ላይ የሚታየው ደብዳቤ ከ USAID የወጣ እንዳልሆነ በመጥቀስ ሀሰተኛነቱን አረጋግጧል።
ተመሳስለው ከሚሰሩ ደብዳቤዎች፣ ዶክመንቶች እንዲሁም ምስሎች እና ቪድዮዎች ራሳችንን እንጠብቅ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
