በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስም እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ ደብዳቤዎች

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስም እየተሰራጩ ያሉ ሀሰተኛ ደብዳቤዎች

ነሐሴ  13፣ 2016

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚን ስም የያዙና ምስላቸው የሚታየው ሁለት ደብዳቤዎች ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወሩ መሆኑን ተመልክተናል።

እነዚህ ደብዳቤዎች በካናዳ ሀገር የስራ እና ትምህርት እድሎችን እናመቻቻለን የሚሉ ይዘቶች ያላቸው ሲሆኑ የተቋማት ‘ማህተሞች’ እንዲሁም የግለሰቦች ስም እና ፊርማዎች አርፈዉባቸዋል።

ከደብዳቤዎቹ መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አቶ ዩሀንስ ብዙነህ ለተባሉ ግለሰብ ውክልና እንደሰጡ የሚገልጽ ነው።

ይህ ውክልናም ለስራ እና ትምህርት ወደ ካናዳ መሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦች ለፓስፖርት እና ቪዛ ወጪ ዮሀንስ ብዙነህ ፍሬው በሚል ስም ወደተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉ የሚጠቅስ ነው።

የዚህን ደብዳቤ ትክክለኛነት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውን መረጃ የጠየቀ ሲሆን እርሳቸውም ደብዳቤው ሀሰተኛ መሆኑን ነግረውናል።

ደብዳቤው በማህበራዊ ትስስር ገጾች መዘዋወር ከጀመረ ወራት መቆጠራቸውን የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የደብዳቤውን ሀሰተኛነት የሚገልጽ መረጃ አጋርቶ እንደነበር ጠቁመዋል።

ሌላኛው ደብዳቤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ‘ማህተም’ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ስም ያረፈበት ሲሆን ብሩህ ተስፋ ኮንሰልታንሲ እና ማፕል ሊፍ ፉድስ የሚሉ ስሞችም ተጠቅሰዋል።

ደብዳቤው “ቪዛቸው በማፕል ሊፍ ፉድስ የጸደቀ እና ያልጸደቀ” በሚል የግለሰቦችን ስም ዝርዝር የያዘ ሲሆን “አቶ መስፍን ተሾመ አክሊሉ የድርጅቱ ባለቤትና ሀላፊ” የሚል ቲተርም ራስጌው ላይ አርፎበታል። ይህ ደብዳቤ የጸሁፍ ግድፈቶች እንዳሉበትም መመልከት ችለናል።

የዚህን ደብዳቤ ትክክለኛነት ለማጣራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑትን አምባሳደር ነብዩ ተድላን መረጃ የጠየቅን ሲሆን እርሳቸውም ጉዳዩ ለምርመራ ወደ ፌደራል ፖሊስ መላኩን ነግረውናል።

ከውጭ ሀገራት የስራ እድል ጋር በተገናኘ በርካታ መረጃዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ሲሆን በተለይ በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስራ እናስቀጥራለን በሚል የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶችም በርካታ ናቸው።

ኢትዮጵያ ቼክም እንደዚህ ያሉ የማጭበርበር ድርጊቶችን ሲያጋልጥ የቆየ ሲሆን የአጭበርባሪዎች ሰለባ እንዳንሆን የስራም ሆነ ትምህርት እደል እናመቻቻለን የሚሉ አካላትን ህጋዊነት ቀድመን እናረጋግጥ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::