ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴ እንደፈረሙበት ተደርጎ እየተሰራጨ ያለ ደብዳቤ ሀሰተኛ ነው

ነሐሴ 1፣ 2016 ዓ.ም
አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴ ለአንድ ግለሰብ ለካናዳ ፓስፖርት፣ ቪዛና መመዝገቢያ ገንዘብ እንዲሰበስብ ውክልና መስጠታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲሰራጭ ተመልክተናል።
ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ስም እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የቀድሞ አርማ በመጠቀም የተጻፈ ደብዳቤ አቶ መስፍን ተሾመ አክሊሉ ለተባሉ ግለሰብ የውክልና የስልጣን ማስረጃ የተሰጣቸው መሆኑን ይገልጻል።
በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ እንደተጻፈ በሚነበበው በዚሁ ደብዳቤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴ ስማቸው ከላይ ለተጠቀሰው ግለሰብ ወደ ካናዳ ለስራና ለትምህርት ዕድል የሚያመለክቱ ሰዎች ለፓስፖርት፣ ለቪዛና ለመመዝገቢያ የሚከፍሏቸውን ክፍያዎች እንዲሰበስቡ ውክልና መስጠታቸውን ይገልጻል። ለዚሁ አገልግሎት እንዲውልም ቁጥሩ 1000627708193 የሆነ የንግድ ባንክ አካውንት ተቀምጧል።
ከደብዳቤው ግርጌም የአምባሳደር ታዬ ነው የተባለ ፊርማ፣ ቲተር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው የተባለ ማህተም ይታያሉ። የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም የፊርማውንና የደብዳቤውን ትክክለኛነት ማረጋገጡን የሚገልጽ ጽሁፍ በደብዳቤው ላይ ይነበባል።
የዚህን ደብዳቤ ትክክለኛነት እንድናጣራላቸውም የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች ጠይቀውናል።
ኢትዮጵያ ቼክ የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ደብዳቤው ሀሠተኛ መሆኑን ገልጾልናል።
በትምህርት፣ በስራ እና በጉዞ ስም ከሚከናወኑ የማጭበርበር ድርጊቶች ራሳችንን እንጠብቅ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





