የሰምሀል መለስን ስም እና ምስል በመጠቀም የተከፈተ ይህ የፌስቡክ አካውንት ሀሰተኛ ነው
ነሀሴ 30፣ 2017
በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ልጅ ሰምሀል መለስ ስም ተመሳስሎ የተከፈተ አንድ የፌስቡክ አካውንት እንዳለ ተመልክተናል።
አካውንቱ አሁን ላይ ከ15 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን አልፎ አልፎ አነጋጋሪ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች በማጋራት በርካታ ግብረ-መልስ (ላይክ፣ ሼር እና ኮመንት) እያገኘ ነው።
ይሁንና ሰምሀል መለስ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጠችው አጭር ቃለ ምልልስ በሷ ስም የተከፈተውና የሷን ፎቶ የሚጠቀመው ‘Semhal A Meles’ የሚለው አካውንት የሷ አለመሆኑን ገልፃለች።
“በጭራሽ ምንም አይነት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች የሉኝም፣ በእኔ ፎቶ እና ስም የተከፈተው Semhal.A Meles የሚባለው የፌስቡክ ገፅ የኔ አይደለም። ከዚህ በፊትም ይሄን ገፅ ለማዘጋትም አንድ ሁለቴ ሞክሪያለሁ” ብላ ሰምሃል ለኢትዮጵያ ቼክ አስረድታለች።
ለማሳያነት ሰምሀል በዚህ ሳምንት ‘Landa Report’ ከተባለ ዩትዩብ ላይ መሰረት ካደረገ የዜና አውታር ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ ትላንትና ሃሙስ ጥዋት በፌስቡክ አካውንቱ መልሶ በማጋራት ትክክለኛ አካውንት ለመምሰል ጥረት ሲያደርግ ተመልክተናል።
ከሀሰተኛ እና ተመሳስለው ከሚከፈቱ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች፣ አካውንቶች እና ቻናሎች ራሳችንን በመጠበቅ ከሀሰተኛ መረጃ ራሳችንን እንጠብቅ።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::