በቀድሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ስም ከተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንት እንጠንቀቅ

በቀድሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ስም ከተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንት እንጠንቀቅ

ሐምሌ 15፣ 2017

በቀድሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ስም እና ምስልን በመጠቀም የተከፈተ የፌስቡክ አካውንት የተለያዩ መረጃዎችን እያጋራ መሆኑን ተመልክተናል።

ይህ አካውንት አሁን ላይ ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን በተከታታይነት በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎችን እያጋራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ቼክ በአካውንቱ ላይ ባደረገው ክትትል በርካታ የአካውንቱ ተከታዮች አካውንቱ ትክክለኛ ነው በሚል እምነት የግለሰቧን ስም ጠቅሰው ሀሳብ እና አስተያየት ሲሰጡ ተመልክተናል።

ይሁን እንጂ የቀድሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ይህ የፌስቡክ አካውንት የእርሳቸው እንዳልሆነ ከወር በፊት በኤክስ (X) ገጻቸው ጽሁፍ አጋርተው ነበር።

ባጋሩት ጽሁፍም “ይህ በእኔ ስም የተከፈተዉ የፌስቡክ አካዉንት የእኔ እንዳልሆነ እና ማንኛዉም በዚህ አካዉንት የሚተላለፍ መልእክት እኔን የማይወክል መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል (https://x.com/ashenafi_meaza/status/1934612702560977203?t=5DWDt90LE3wmOmfcEWSZMg&s=19)።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ላቀረበው ጥያቄም ይህ ሀሰተኛ አካውንት መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ምንም እንኳ ይህ አካውንት ከሚያጋራቸው ይዘቶች አንጻር አጠራጣሪ ቢሆንም የተከታዮቹ ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተመልክተናል።

የግለሰቦች እንዲሁም ተቋማትን ስም፤ ምስል ወይም አርማ በመጠቀም የሚከፈቱ ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እና አካውንቶች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ አካውንቶች እና ገጾችን ከመከተላችን በፊት ትክክለኛነታቸውን እናረጋግጥ።

አጠራጣሪ በሆኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እና አካውንቶች የሚጋሩ መረጃዎችንም ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::