የግብጽ ሚዲያዎች በታላቁ የሕዳሴ ግድብ አቅራቢያ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ በማለት ያሰራጩት መረጃ የተሳሳተ ነው
መስከረም 18፣ 2017 ዓ.ም
አንዳንድ የግብጽ ሚዲያዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቅርብ ርቀት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የሚገልጹ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውን ተመልክተናል።
መረጃውን ካሰራጩት መካከል ኢጅፕት ኢንዲፔንደንት (Egypt Independet) እና ፋሃርስ ኒውስ (Fahars News) የሚገኙበት ሲሆን መጠኑም በሬክተር ስኬል 5.0 እንደሚጠጋ አስነብበዋል። ለዘገባቸውም ‘Strikes’ እና ‘Rocks’ የሚሉ ከባድ ቃላቶችን መጠቀማቸውን አስተውለናል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት የግብጽ ሚዲያዎች ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጧል።
መረጃውን ለማጣራት ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂዮ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አየለ የመሬት መንቀጥቀጡ የተመዘገበው በአፋር ክልል መሆኑን ገልጸው ከህዳሴ ግድብ በጣም እንደሚርቅና በግድቡ ላይ ምንም አይነት ተጽኖ እንደሌለው አብራርተዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡም በሬክተር ስኬል 4.5 ነበር ብለዋል።
በተመሳሳይ በመላው አለም የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን የሚከታተለው ኧርዝኩዌክ ፊድ (Earthquake Feed) ድረገጽ ክስተቱ የተመዘገበው ባለፈው ሀሙስ ከአዋሽ በስተሰሜን ምዕራብ መሆኑን አረጋግጦ መጠኑም 4.5 መሆኑን መዝግቧል።
የግብጽ ሚዲያዎች የህዳሴ ግድብ የመሬት መንቀጥቀጥ ስጋት እንዳለበት በተደጋጋሚ እንደሚያስነብቡ የሚታወቅቢሆንም የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋቱ ትክክል አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::