“የፋኖ ሀይሎች ሚሳኤል የታጠቀ ድሮን በአማራ ክልል መተው ጣሉ” በሚል እየተሰራጨ የሚገኝ ቪድዮ የቆየ ነው
ጥቅምት 13 2017 ዓ.ም
ሰሞኑን በፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ተመቶ የወደቀን የጦር ድሮን ያሳያል በሚል አንድ ቪድዮ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወረ ይገኛል።
ይህ የስክሪን ቅጂው (screenshot) የሚታየውን ቪድዮ አማራ ክልል ውስጥ እንደተቀረጸ በመጥቀስ ካጋሩት መካከል ደጎሞ በኤክስ (X) ከ159 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Bashir Hashi Yussuf’ የሚል ስም ያለው አካውንት ይገኝበታል፡ https://x.com/BashirHashiysf/status/1848176849576194085?t=aw7ptfy0vZz5VjSzf21aMg&s=19
በ‘Bashir Hashi Yussuf’ አካውንት የተጋራውን የጽሁፍ እና ቪዲዮ መረጃም ከ100 በላይ የኤክስ ተጠቃሚዎች መልሰው አጋረተውታል።
በርግጥ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰከሰን የጦር ድሮን የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጻፈ እንደሚገኘው በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች ተመቶ የወደቀ አይደለም።
ኢትዮጵያ ቼክ 36 ሴኮንዶች በሚረዝመው ቪዲዮ ላይ ባደረገው ማጣራት ቪዲዮው ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተከሰከሰ ድሮንን የሚያሳይ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህ ድሮን ግንቦት 2016 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተከሰከሰ ሲሆን በወቅቱም በማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በርከት ያሉ ሚዲያዎች ሽፋንም አግኝቶ ነበር።
በወቅቱ የተከሰከሰውን ድሮን የሚያሳይ እና ከሁለት ደቂቃ በላይ ርዝመት ያለው ቪዲዮ በስፋት ተጋርቶ ነበር፡ https://x.com/finfinne_time/status/1793418212908188130?s=46&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ
በተጨማሪም ቢቢሲ ስለ ክስተቱና በተንቀሳቃሽ ምስሉ ስለሚታየው ድሮን ዘለግ ያለ ትንታኔ አስነብቦ ነበር፡ https://www.bbc.com/amharic/articles/c999lygqz7vo.amp
ትክክለኛ ምንጫቸው ሳይጠቀስ ከሌላ ቦታ ተወስደው፤ አሁን የተከሰተን ሁኔታ ያሳያሉ በሚል የሚጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ለተሳሳተ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::