አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነት ሆነው ተመርጠዋል?

መጋቢት 9፣ 2015 ዓ.ም
“አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነት ሆነው ተመርጠዋል” እንዲሁም “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸው ይፋ ተደርጓል” የሚሉ መረጃዎች ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ባደረገው ማጣራት አቶ ጌታቸው በፓርቲያቸው (ህወሓት) ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትነት ቦታ መታጨታቸውን እንጂ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሆነው ስለመመረጣቸው የተሰራጨው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ አረጋግጧል።
“ጉዳዩ ሂደቱን ጨርሶ አላለቀም፣ አቶ ጌታቸው ግን የታጩበትን ቦታ እንደሚያገኙ በስፋት ይጠበቃል” ብለው ቃላቸውን ለኢትዮጵያ ቼክ የሰጡ አንድ የህወሀት ከፍተኛ አመራር “ሂደቱ በቅርብ ሳምንታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።
የትግራይ ቴሌቭዥን የአቶ ጌታቸውን በህወሀት መመረጥ ዛሬ ጠዋት በፌስቡክ ገፁ አስነቧል።
በዚህ ዙርያ ዜናውን ያጋራው ቪኦኤ ይህንን ያረጋገጠ ሲሆን “የአቶ ጌታቸውና ሌሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ሹመት የክልሉ አመራሮች ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በጊዜያዊ አስተዳደሩ አወቃቀር ጉዳይ ተወያይተው ካፀደቁት በኋላ” እንደሚሆን ጠቁሟል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
