“መቐለ ዩኒቨርሲቲ በሚቀጥለው ሳምንት ስራ ይጀምራል የሚለው ዜና የተሳሳተ ነው”- መቐለ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ቼክ

መጋቢት 4፣ 2015 ዓ.ም
በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት የመማር ማስተማር ሥራው የተቋረጠው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሥራውን እንደሚጀምር የ “Tigray Today/ትግራይ ቱደይ” የፌስቡክ ገጽ በትናንትናው እለት ዘግቧል።
ከ138 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት ገፁ ባሰራጨው መረጃ መሰረት ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት አራት ወራት 24,000 የሚጠጉ የቀድሞ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ እና ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ይገልፃል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት በኩል የሚያስፈልግ በጀት ሁሉ ተለቆለታል ሲል “መልካም ዜና” በሚል ባሰራጨው ዘገባ ጠቅሷል።
መረጃውን እስከ አሁን ከ2,400 በላይ ሰዎች ላይክ አርገዋል፤ ከ373 በላይ ሰዎች ደግሞ አጋርተውታል፣ በርካታ ሌሎች ገፆች እና የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም አጋርተውታል።
ነገር ግን ይህ መረጃ ሀሰት መሆኑን የዩኒቨርስቲው ሰራተኞች እና አመራሮች ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል። መቐለ ዩኒቨርሲቲም ይህንን ዜና የሚመለት መረጃ በይፋዊ የፌስቡክ እና የትዊተር አካውንቱ ላይ አላወጣም።
የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሓጎስ ዩኒቨርሲቲው ስራ ለመጀመር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የራሱን ጊዜና ሂደት ይወስዳል ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጡት መረጃ ተናግረዋል።
“ሥራውን ይጀምራል፤ ነገር ግን በሚቀጥለው ሳምንት አይደለም። በእርግጥ ይህንን ለማድረግ ወራትን ይፈጃል” ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን ለተማሪዎቹ ያቀረበው ጥሪ እንደሌለ በመግለጽ “እኛ (ዩኒቨርሲቲው ወይም የትምህርት ሚኒስቴር) ተማሪዎቻችንን እንደገና ለመቀበል ዝግጁ ስንሆን ይፋዊ መግለጫ እንሰጣለን” ብለዋል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
