በስማቸው የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶችን በተመለከተ አሰልጣኝ ረ/ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ ለኢትዮጵያ ቼክ የሰጡት ምላሽ

ነሐሴ 19፣ 2015 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ብሄራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ ስም የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶችን ትክክለኛነት እንድናጣራ ከተከታዮቻችን ጥቆማ ደርሶናል።
ይህ ጥቆማ ምስሉ በሚታየው አካውንት ሰሞኑን ሲጋሩ የነበሩ መረጃዎችን መሰረት ያደረገ እንደሆነም መረዳት ችለናል።
ይህ የአሰልጣኝ ረ/ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦን ስም እና ምስል በመጠቀም የተከፈተ አካውንት ባለፉት ሳምንታት በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር የተገናኙ መረጃዎችን አጋርቶ ነበር።
ይሁን እንጂ በአካውንቱ ተጋርተው የነበሩ የተወሰኑ መረጃዎች ከአካውንቱ ላይ መነሳታቸዉንም ተመልክተናል።
ኢትዮጵያ ቼክ ይህን አካውንትና ሌሎች በስማቸው የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶችን በተመለከተ ለአሰልጣኝ ረ/ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን አካውንቱም ሆነ በአካውንቱ የተጋሩ መረጃዎች የእርሳቸው እንዳልሆኑ ነግረውናል።
በተጨማሪም አሰልጣኙ “የራሴ አካውንት የለኝም፤ ተጠቅሜም አላውቅም” ያሉ ሲሆን አሁን ላይ እየተጠቀሙበት ያለ የፌስቡክ አካውንት እንደሌላቸው ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
