ኢቢሲ አሳሳች በሆነ መልኩ የሰራው የፍርድ ቤት ክስ ሂደት ዘገባ

ግንቦት 9፣ 2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በትናንትናው እለት “ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው” የሚል አሳሳች ዜና መስራቱን ተመልክተናል።
ተቋሙ በዚህ ዘገባው የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት እና ሌሎች 14 ግለሰቦች ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ በመመዝበር ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ዘገባ ሰርቷል።
ኢትዮጵያ ቼክ የፍትህ ሚኒስቴርን መግለጫ እንዲሁም የክስ ሰነዱን የተመለከተ ሲሆን የኢቢሲ ዘገባ አሳሳች እንደሆነ ታዝቧል።
ፍትህ ሚኒስቴር በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ትናንት ያወጣው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ “ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ ህገ-ወጥ ግዥ በመፈፀም በሙስና ወንጀል እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ክስ ተመሰረተባቸው” የሚል መረጃ አጋርቷል።
በዚህም መሰረት ተጠርጣሪዎቹ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ከህግ አግባብ ውጭ ግዢ እንደፈፀሙ እና ሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎችን ፈፅመዋል ተብለው እንደተጠረጠሩ ገለፀ እንጂ ኢቢሲ እንደዘገበው ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ በመመዝበር እንደተጠረጠሩ አይገልፅም። ይህም ክሱ በተጋነነ መልኩ እንዲቀርብ እንዳደረገው መመልከት ችለናል።
በተጨማሪም የፍትህ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ “ተከሳሾች ከፍርድ በፊት እንደ ንጹህ የመገመት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው የተጠበቀ ነው” የሚል የተለመደ የፍትህ ስርዐት አካሄድን ቢጠቅስም የኢቢሲ ዘገባ ተጠርጣሪዎቹን ከብያኔ በፊት የመፈረጅ አዝማሚያ እንዳለው ማየት ይቻላል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
