ይህ ቪድዮ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ወቅት የተቀረፀ አይደለም

ነሐሴ 11፣ 2015 ዓ.ም
ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት በአፋን ኦሮሞ ‘jaalattus jibbitus abbaan biyyaa Oromoodha’ ወይም በአማርኛ ትርጉሙ “ወደድክም ጠላክም ባለ ሀገሩ (የሀገሩ ባለቤት) ኦሮሞ ነው” በማለት ሲጨፍሩ ያሳያል የተባለ ቪድዮ በስፋት ሲሰራጭ ተመልክተናል።
ይህ ቪዲዮ በፌስቡክና ቲክቶክ በተደጋጋሚ የተጋራ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠር ግብረ መልስ ማግኘቱንም አስተውለናል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት በተጋራው ቪዲዮ ላይ የሚታዩት ወታደሮች እና በቪዲዮው የሚሰማው የዘፈን ድምጽ ከዚህ በፊት በተለያዩ አውዶች በተናጠል መልኩ በተደጋጋሚ ሲጋሩ የቆዩ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ለምሳሌም ወታደሮቹ አርቲስት ጫላ ቡልቱሜ ስለ መከላከያ ሠራዊት በዘፈነው የኦሮምኛ ሙዚቃ ሲጨፍሩ የሚታዩበት ተመሳሳይ ቪዲዮ በቲክቶክ ከወር በፊት መጋራቱን ተመልክተናል። ቪዲዮውን ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል መመልከት ይቻላል: https://vm.tiktok.com/ZM2EHGht7/
በተመሳሳይ በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ወታደሮች የስክሪን ቅጂ ከሁለት አመት በፊት በትዊተር (በአሁን መጠርያው ኤክስ) ተጋርቶ እንደነበርም አይተናል። የስክሪን ቅጂውን ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል መመልከት ይቻላል: https://twitter.com/4_woreda/status/1451489183588028417?s=19
እንዲሁም በቪዲዮው የሚደመጠው ዘፈን Finfinnee Free Post በተባለ የፌስቡክ ገጽ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ተጋርቶ እንደነበር ተመልክተናል። የፌስቡክ ገጹ ባጋራው ቪዲዮ ሲጨፍሩ የሚታዩትም ወታደሮች ሳይሆኑ ወጣቶች ናቸው። ቪዲዮውን ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል መመልከት ይቻላል: https://fb.watch/mtTBL2-B0b/?mibextid=Nif5oz
እነዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ከሰሞኑ እንደሆነ ተደርጎ የቀረበ የቪድዮ እና ድምፅ ቅንብር ቆየት ያለ እና ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያያዥነት የሌለው እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ማህበራዊ ሚድያ ላይ ከአውድ ውጪ ከሚቀርቡ ሀሰተኛ የፅሁፍ፣ የምስል፣ የድምፅ እንዲሁም የቪድዮ መረጃዎች ራሳችንን እንጠብቅ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
