ድምጽ ማቸገን (voice cloning) ምንድ ነው? ጉዳቱስ? እንዴት መከላከል እንችላለን?

ድምጽ ማቸገን (voice cloning) ምንድ ነው? ጉዳቱስ? እንዴ መከላከል እንችላለን?

ኀዳር 19፣ 2017

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅዎች ፈጣንና የማያቋርጥ እድገት ለሰው ልጆች በርከት ያሉ ዕድሎችን ይዘው ስለመምጣታቸው በተደጋጋሚ ሰምተናል። በአንጻሩ ቀላል የማይባሉ ጉዳቶችን እያስከተሉ ስለመሆናቸውም አድምጠናል። ለምሳሌም በእነዚህ ቴክኖሎጅዎች የሚፈበረኩ ምስሎች፣ ቪዲዮዎች እና ጽሁፎች የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን በማባባስ ረገድ በመጫዎት ላይ ያሉትን አሉታዊ ሚና መጥቀስ ይቻላል።

አሁን አሁን ደግሞ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ አማካኝነት የሚሰሩ የተቸገኑ ድምጾች (Voice cloning) በመላው ዓለም መነጋገሪያ መሆናቸውን ተመልክተናል።

ድምጽ ማቸገን ወይም የሰዎችን ድምጽ ናሙና በመውሰድ ተመሳሳይ ድምጾችን ማምረት በጣም ቀላልና ከሶስት ሰከንድ ያነሰ የድምጽ ናሙና በመውሰድ ብቻ ሊሰራ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከተወሰደው የድምጽ ናሙናም ተመሳስሎ ሊሰራ የታሰበውን ሰው የአነጋገር ዘየ፣  ቅላፄ፣ የአተነፋፈስ ስርዐትንና ወዘተ በመቅዳት ፍጹም ለመለየት በሚያስቸግር አግባብ ተመሳሳይ ድምጽ ይፈበረካል።

እንዲህ ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ግኝቶች እንደህክምና ባሉ ዘርፎች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑ ቢነገረም ለማጭበርበር ድርጊት ብሎም ሀሠተኛ መረጃን ለማሰራጭት በስፋት ጥቅም ላይ መዋል መጀመራቸው ብዙዎችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።

በድምጽ ማቸገን አማካኝነት የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች በመላው ዓለም ዕለታዊ የዜና አርዕስት እየሆኑ ሲሆን ለምሳሌ የአሜሪካዎቹ የፌራል ምርመራ ቢሮና የሳይበርና መሰረተ ልማቶች ደህንነት ኤጀንሲ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ በእንዲህ ያለው ወንጀል በሀገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አጽንኦት ሰጥተውበታል። ከአለፈው አመት ጋር ሲነጻጸርም በደምጽ ማቸገን የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች በያዝነው የፈረንጆች አመት በከፍተኛ መጠን ማሻቀባቸውን ገልጸዋል።

ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ወንጀለኞች ሊያጠቁ ከፈለጉት ሰው የስራ ሀላፊ ወይም ባልደረባ፣ የትዳር አጋር፣ ልጅ ወይም ሌላ የቅርብ ሰው የድምጽ ናሙናን ይወስዳሉ። የድምጽ ናሙናውን ከዩቱብ፣ ከቲክቶክ፣ ከስልክ ምልልስ አልያም ከሌላ ቦታ ሊያገኙት ይችላሉ። ቀጥሎም በተፈበረከው ድምጽ አማካኝነት ስልክ በመደወል የማጭበርበር ድርጊቱን ይፈጽማሉ።

እንዲህ አይነቱን በጣም አሳሳች የማጭበርበር ድርጊት ለመለየት አስቸጋሪ ሲሆን በመጀመሪያ ማድረግ የምንችለው ነገር ድምጽ ማቸገን እንደሚቻል ማወቅን ነው። ይህን ካወቅን አጠራጣሪ እና ያልተለመዱ፣ አስቸኳይና ገንዘብ የሚጠይቁ የድምጽ መልዕክቶችን ስንቀበል ቆም ብለን ማሰብ እና ለማጣሪያ የሚሆኑ ጥያቄዎችን ማቅረብ ይሆናል።

የድርጊቱ ኢላማዎች ተቋማት ከሆኑ ደግሞ ከተደወለው ስልክ የሚሰማው ድምጽ በቀጥታ ንግ ግር የሚሰማ ነው ወይም ተቀርጾ የሚተላለፍ ነው የሚለውን ለማጣራት የሚረዱ ቴክኖሎጅዎችን ስለመጠቀም ማስብ መጀመር ይኖርባቸዋል። የሚቸገኑ ድምጾች ተቀርጸው የሚተላለፉ ስለሆነ ይህን መለየት የሚችሉ ሶፍትዌሮችን መጠቀም ይቻላል።

ለአጭበርባሪዎች እንዳንጋለጥ ሁሌም ጥንቃቄ እናድርግ!

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::