ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መቼ ይጀመር ይሆን?

በርካታ ያደጉ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለዜጎቻቸው መስጠት ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የክትባቱ ምርምር ገና በላቦራቶሪ ሂደት ላይ እያለ ከመድሀኒት አምራች ድርጅቶች ጋር ውል የፈፀሙት እነዚህ ሀገራት አሁንም በበቂ አቅርቦት እና ፍጥነት ክትባቱን መስጠት ባይችሉም እንደ እስራኤል ያሉ ሀገራት ወደ ግማሽ የሚጠጋ ወይም ከግማሽ ያለፈ ህዝባቸውን መከተብ ችለዋል።

በተቃራኒው ይህን ግዢ መፈፀም ያልቻሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ክትባት መጀመር አልቻሉም፣ ይልቅስ በ Gavi Alliance ስር የሚንቀሳቀሰው እና ክትባቱን ለማዳረስ በሚሰራው COVAX በተባለው ፕሮግራም ተስፋ ጥለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ አዳጊ ሀገራት ደግሞ ከዚህ ፕሮግራም በተጨማሪ ከሌሎች ሀገራት ተጨማሪ ክትባቶችን ለማግኘት ጥረት እያረጉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በያዝነው አዲሱ የፈረንጆች አመት ማብቂያ (ከአስር ወር በሁዋላ) 20 ፐርሰንት የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ ማቀዷን በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ዮሀንስ በቅርቡ ተናግረው ነበር። እንደ አቶ ሙሉቀን ገለፃ ሀገሪቱ ይህን ለማሳካት ከአለም ባንክ 16 ቢልዮን ብር ጠይቃለች። “ይህም ላይበቃ ይችላል፣ ግን ተጨማሪ ድጋፍ ከሌላ አካል ይፈለጋል” ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ለክትባት የምታውላቸው 9 ሚልዮን የኮሮና ቫይረስ የክትባት ብልቃጦችን ከአንድ ወር በሁዋላ ትረከባለች ብለዋል። በዚህ ግዜም የጤና ባለሙያዎች እና በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ቅድሚያ ያገኛሉ ብለዋል።

በስራ ሀላፊዎች ይህ ቢነገርም ክትባቱን ማግኘት ግን እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ አለም አቀፍ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። የፋይዘር፣ ሞደርና እና አስትራ-ዜንካ ክትባቶች ሙሉ ለሚሉ በሚባል መልኩ ምርቶቻቸውን ቅድሚያ ላዘዙ ሀብታም ሀገራት እያከፋፈሉ ሲሆን የቻይናው ሳይኖ ፋርም እና የሩስያው ስፑትኒክ ክትባቶች ደግሞ የምርት መጠናቸው፣ አንዳንድ ግዜ ደግሞ ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ይታያል።

ክትባት ለመስጠት የሚፈልጉ ሀገራትም ከጥቅም ትስስር ጋር ሲያያይዙት ይታያል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ እና አልጄርያ ክትባት ለመስጠት መዘጋጀቷን ገልፀው “የቻይና ጥቅሞችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሀገራቱ ድጋፍ እንደምናገኝ ተስፋ እናረጋለን” ብለዋል።

እንዲሁ እስራኤል ትርፍ ክትባቶችን ለማከፋፈል የሀገራት ዝርዝር እያዘጋጀች እንደሆነ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ ምክትል አምባሳደር ኦር ዳንኤሊይ ገልፀው “ኢትዮጵያ ዝርዝሩ ውስጥ ትኑር፣ አትኑር አሁን ማወቅ አይቻልም” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራት የCOVAX ፕሮግራም ከፍ ያለ ተስፋ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ክትባት የሚጠባበቁ 92 ሀገራት በስሩ ስላሉ የክትባት አቅርቦት እጥረት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ከሁለት ቀን በፊት ጋና በፕሮግራሙ የመጀመርያዋ ተጠቃሚ ሀገር ስትሆን በመጀመርያ ዙር 600,000 የአስትራ-ዜንካ ክትባቶችን ተረክባለች። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀጋራት ተስፋ ሰጥቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::