ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ሀገራት አባል እንድትሆን ጥሪ ቀረበላት እንጂ አሁን ላይ ቡድኑን አልተቀላቀለችም

ነሐሴ 18፣ 2015 ዓ.ም
በርካታ በተለይ የመንግስት የሆኑ ሚድያዎች “ኢትዮጵያ ብሪክስን ተቀላቀለች” እና “ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆነች” የሚሉ መረጃዎችን እያጋሩ እንደሆነ ተመልክተናል።
ለምሳሌ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዛሬው ዘገባው “በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ፥ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን በአዲስ አባልነት ተቀብሏል… ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገራትን ተቀላቅላለች” ብሎ አሳሳች መረጃ አጋርቷል።
ኢትዮጵያ ቼክ የስብሰባው አዘጋጅ የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሳይሪል ራማፎዛ በትዊተር (ኤክስ) አካውንታቸው ላይ በዚህ ዙርያ ያሰፈሩትን መረጃ የተመለከተ ሲሆን ብሪክስ መስፋት ባለበት ዙርያ ምክክር ተደርጎ “በመጀመርያው ዙር አርጀንቲና፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከጃንዋሪ 1 2024 (ታህሳስ 22/2016) ጀምሮ ሙሉ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል” ብለዋል። ሊንክ: https://twitter.com/CyrilRamaphosa/status/1694618085783720092?t=5iBu0o_FKrL2s7oI3KixBg&s=19
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት የብሪክስ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበላቸው እንጂ አሁን ላይ ቡድኑን እንዳልተቀላቀሉ መረዳት ይቻላል፣ ይህም ከላይ የተጠቀሱት የመንግስት ሚድያዎች ያሰራጩት መረጃ አሳሳች እንደሆነ ማየት ይቻላል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው እ.አ.አ ሰኔ 29/2023 ነበር።
በተያያዘ መልኩ ፋና በዘገባው “ብሪክስ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ እስከ ፈረንጆቹ 2050 የዓለምን ምጣኔ-ሐብት ለመቆጣጠር ግብ አስቀምጧል” የሚል መረጃ ቢያጋራም ይህም የግለሰቦች እና ተንታኞች ምልከታ እንጂ የብሪክስ ቡድን “የ2050 ግብ ምልከታ” ላይ እንደማይገኝ ለማየት ችለናል።
ብዙ ተከታታይ ያላቸው ሚድያዎች መረጃዎችን ከማጋራታቸው በፊት ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል ላይ ሊሰሩ ይገባል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
