ይህ ምስል ሰሞኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባህርዳር ‘የተጓጓዙ’ የመከላከያ አባላትን አያሳይም
መስከረም 27፣ 2018
‘ትግራይ ኩሕሎ’ የሚል ስም እና ከ75 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ መስከረም 26/2018 ቀን ሙሉ ወታደሮችን ወደ ባህርዳር ከተማ እያጓጓዘ ነው” የሚል መረጃ በትናንትናው ዕለት አጋርቷል።
ገጹ ይህን መረጃ ከምስል ጋር ያጋራ ሲሆን በምስሉም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይታያሉ።
በገጹ የተጋራዉን የጽሁፍ እና ምስል መረጃ ከ300 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሀሳብ እና አስተያየት የሰጡበት ሲሆን ከ70 በላይ ተጠቃሚዎች መልሰዉ አጋርተዉታል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሉ ከቪዲዮ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ ሲሆን ባለፉት አመታት በተደጋጋሚ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲጋራ የነበረ መሆኑን ተመልክቷል።
ይህ ምስል የተወሰደበትን ቪዲዮ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሕብረት’ የሚል ስም ያለው ገጽ አንዱ ሲሆን ቪዲዮዉን ከ2 ዓመታት በፊት አጋርቶ ነበር፡ https://www.facebook.com/watch/?v=2250405228501839&vanity=100064848901912
በተጨማሪም ‘The Habesha’ የተሰኘ ድረ-ገጽ ምስሉን በተለያዩ ጊዜያት የተጠቀመ ሲሆን ከዓመት በፊት የሀገር ዉስጥ የአየር ጉዞን በተመለከተ ለሰራዉ ዘገባ ተጠቅሞበት ነበር፡ https://zehabesha.com/sharp-increase-in-domestic-air-travel-gains-and-pains/
እነዚህ የቆዩ ምስሎች ከአውድ ውጪ የቀረቡ ቢሆንም በቅርብ ቀናት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ የመንግስት ሀይሎች እንቅስቃሴ እያረጉ እንደሚገኝ የተለያዩ ሚድያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።
የቆዩ እና ምንጫቸው ሳይጠቀስ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::