አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ከሰሞኑ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፅም ከታየው ግለሰብ ጋር ተቀምጠው የሚያሳየው ምስል ትክክለኛ ያልሆነ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ከሰሞኑ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፅም ከታየው ግለሰብ ጋር ተቀምጠው የሚያሳየው ምስል ትክክለኛ ያልሆነ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

ህዳር 17፣ 2018

ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ የፋኖ ታጣቂዎች አባል እንደሆነ የተገለጸ ግለሰብ የአንድን ግለሰብ እጅ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሲቆርጥ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል።

ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘም የድርጊቱ ፈጻሚ ግለሰብ ምስሎች ናቸው በሚል የተለያዩ ፎቶዎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።

ከነዚህ መካከል ደግሞ በስክሪን ቅጂው (screenshot) ላይ የሚታየውና ግለሰቡ ከአንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም ከለበሰ ግለሰብ ጋር ‘ተቀምጦ ሲያወሩ ያሳያል’ በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጨ ምስል ይገኝበታል።

ይህ ምስል “እውነት እያደረች ትጠራለች ተደብቃ አትቀርም! የጨካኙ የብልፅግና ድራማ በማስረጃ ተጋልጧል” የሚል ጽሁፍም ይዟል። ይህም በጭካኔ ድርጊቱ የመንግስት እጅ እንዳለበት ህዝብን ለማሳመን የተደረገ ሙከራ እንደሆነ አንዳንዶች ሲገልፁ ተስተውለዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ትክክለኛ ያልሆነ እና በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተሰራ እንደሆነ አረጋግጧል።

ምስሉን ለማጣራት የጉግል ምርት የሆነዉን ሲንት አይዲ ዲቴክተር (SynthID Detector) የተጠቀምን ሲሆን መገልገያዉም ምስሉ በጉግል ኤአይ (Google AI) የተሰራ እንደሆነ አመላክቷል።

በሌላ በኩል የአሰቃቂ ድርጊቱን እንደፈጸመ እየተነገረ የሚገኘውን ግለሰብ በተመለከተ የተለያዩና የሚቃረኑ ሀሳቦች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወሩ እንደሚገኙም ተመልክተናል።

ከመንግስት በኩል በጉዳዩ ዙርያ እስካሁን አስተያየታቸውን ከሰጡት መሀል የጠ/ሚር አብይ አህመድ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይገኙበታል።

“ተይዘው የመጡት ስልኮች ብዙ ነገር እየነገሩን ነው” በማለት ቪድዮው ከተያዙ ታጣቂዎች እንደተገኘ የጠቆሙ ሲሆም ታጣቂዎቹ ከማን ጋር እንደሚገናኙ፣ ማን ገንዘብ እንደሚልክላቸው፣ እነማንን እንደ ደፈሩ፣ እነማንን እንደ ገደሉ፣ እነ ማንን እንዳገቱ፣ ብዙ ብዙ ነገር እየነገሩን ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የፋኖ አመራሮች ድርጊቱን ሲፈፅም የሚታየው ግለሰብ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ (November 12, 2025) ለመንግስት እጅ እንደሰጠ በአማራ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በኩል መገለፁን ያነሳሉ። ድርጊቱ መቼ እንደተፈፀመ ባይጠቅሱም ከሰሞኑ ቢቢሲ በዘገባው ያወጣውን በአማራ ክልል የተፈፀመ የሴቶች መደፈር ዜና ለማደብዘዝ ሆን ተብሎ የተቀናበረ እንደሆነ ሲናገሩም ተደምጠዋል።

ይሁንና ከላይ የተጠቀሰው ምስል ሀሰተኝነት በመረጃ ማጣርያ ዴስካችን በኩል ተረጋግጧል።

በመሆኑም በእንደዚህ አይነት ጊዜ ለሚሰራጩ ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እንዳንጋለጥ ተአማኒ ባልሆኑ ምንጮች የሚጋሩ አጠራጣሪ መረጃዎችን፣ ምስሎችን እና ቪድዮዎችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::