የሩስያው ፕሬዝደንት በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዙርያ ሰጡት የተባለው አስተያየት ምን ያህል እውነትነት አለው?

ጥቅምት 19፣ 2018
አንዳንድ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የሩስያው ፕሬዝደንት ቭላዲሚር ፑቲን በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዙርያ ከሰሞኑ አስተያየት ሰጥተዋል በማለት አንዳንድ መረጃዎችን እያስተላለፉ ይገኛሉ።
‘ዲጂታል ኢትዮጵያ’ እና ‘Ahmed Habib Alzarkawi’ የተባሉ በርካታ ተከታይ ያላቸው ገፆች “እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ህዝብ ያላትን ትልቅ ሀገር የባህር በር ከልክሎ የቀጣናው ሀገራት ያድጋሉ እንዲሁም ቀጠናው ሰላም ይሆናል ማለት ሞኝነት ነው። ይልቅ የቀጠናው ሀገራት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ቢተባበሩ ቢጥሩ ይሻላል” በማለት ፑቲን እንደተናገሩ ተመሳሳይ የሆነ መረጃ አጋርተዋል።
ሁለቱም ገፆች ፑቲን ይህን ንግግረ መቼ እና የት እንዳደረጉ አልገለፁም።
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ባደረገው ማጣራት መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል፣ የትኛውም ሚድያ እንዲሁም መንግስታዊ የመረጃ አካል ይህን እንዳላወጣ ተመልክተናል።
ስፑትኒክ የሚባለው መንግስታዊው የሩስያ የሚዲያ ተቋም ለኢትዮጵያ ብሎ በከፈታቸው የኤክስ እና የቴሌግራም ገፆቹ ላይ ፕሬዝደንቱ ተናገሩት የተባለውን መረጃ አልዘገቡም።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ መንግስት በሚያስተዳድራቸው የድረ-ገፅ፣ ህትመት፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሚዲያ ተቋማት ላይ ፕሬዝደንት ፑቱን ሰጡት የተባለውን አስተያየት አላወጡም።
እንዲሁም ፑቲን ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተናገሩት የተባለው አስተያየት በቪዲዮም ሆነ በድምፅ የቀረበ ማስረጃ የለም።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ትናንት ማክሰኞ ፓርላማ ላይ የሰጡት መግለጫ የአገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ቀርበው የመንግስታቸውን ስራ አፈፃፀም ባስረዱበት መድረክ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በርካታ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ ኢትዮጵያ በህግ እና በንግግር እንዲፈታ በተናጠል ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ለሩስያ፣ ለአውሮፓ ሀገራት እና ለሌሎች ሀገራት ጥያቄ እንዳቀረቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንትና በነበራቸው የፓርላማ ውሎ ላይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄያቸው ሩስያን ጨምሮ ከነዚህ ሀገሮች ያገኟቸው መልሶች እንዳለ የጠቀሱት ነገር የለም።
ምንጫቸው ሳይገለፅ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች ለተሳሳቱ እና ሀሰተኛ ለሆኑ መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
