አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአሜሪካ ፓርኪንግ ሲሰሩ ያሳያል በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተጋራ የሚገኘዉ ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአሜሪካ ፓርኪንግ ሲሰሩ ያሳያል በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተጋራ የሚገኘዉ ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

ጥቅምት 4፣ 2018

በርካታ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች “አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአሜሪካ ፓርኪንግ ሲሰሩ ያሳያል” በሚል በስክሪን ቅጂው (screenshot) ላይ የሚታየውን ምስል እያጋሩ ይገኛሉ።

ይህን መረጃ እና ምስል ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘Arada Times’ የሚል ስም ያለው እና ከ44 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ አንዱ ነው። ይህ ገጽ ያጋራዉን ጽሁፍ እና ምስል ከ130 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰዉ ያጋሩት ሲሆን ከ1,600 በላይ ሰዎች ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተዉበታል።

በተጨማሪም ‘Ethio Times’ የተባለ ከ1 ሚልዮን በላይ ተከታይ ያሉት የፌስቡክ ገፅም ምስሉን አጋርቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሉ ትክክለኛ ያልሆነ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ መሆኑን አረጋግጧል።

የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት በጉግል ኤአይ (Google AI) የተሰሩ ምስል፤ ድምጽ እና ቪዲዮዎችን ለማጣራት የሚያገለግለው እና በጉግል የተበለጸገዉን ‘SynthID Detector’ የተጠቀምን ሲሆን ምስሉም በጉግል ኤአይ ምርት የተሰራ መሆኑን ተመልክተናል።

ጉግል በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰሩ ምስሎች፤ ድምጾች እና ቪዲዮዎች አማካኝነት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ‘SynthID Detector’ የተሰኘዉን መገልገያ ያበለጸገ ሲሆን መገልገያዉም በGemini፣ Imagen፣ Lyria እና Veo ሞዴሎች የተመረቱ ምስሎች፣ ድምጾች እና ቪዲዮዎችን ለማጣራት ይረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ በምስሉ ላይ የሚታዩት የድሮ ሞዴል ፎርድ ስሪት የሆኑ ቢጫ ታክሲዎች ከጥቂት አመታት ወዲህ ከአሜሪካ መንገዶች ላይ እንደማይታዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአሁኑ ወቅት ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መስፋፋት እና መርቀቅ ጋር በተያያዘ ትክክለኛ የሚመስሉ እና ለመለየት አዳጋች የሆኑ የድምጽ፣ ምስል እና ቪዲዮ ይዘቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስራት ማሰራጨት በጣም ቀላል ሆኗል።

በመሆኑም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የምንመለከታቸዉን እና ታማኝ ባልሆኑ የመረጃ ምንጮች የሚሰራጩ የምስል እና ቪዲዮ ይዘቶችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::