‘በአለም አቀፍ ደረጃ የወንዶች ቁጥር በመቀነሱ እጥረት ገጥሟል’ በሚል ስለተሰራጨው መረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት /UN/ መረጃ ምን ይላል?
ነሀሴ 20፣ 2017
በርካታ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች “በአለም አቀፍ ደረጃ የወንዶች ቁጥር መቀነሱ እና እጥረት መግጠሙ ተዘገበ” የሚል መረጃ እያሰራጩ ይገኛሉ።
እነዚህ የመረጃ ምንጫቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት /UN/ እንደሆነ የጠቀሱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በያዝነው አመት እኤአ 2025 በአለም ላይ 7.8 ቢሊዮን ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህ ዉስጥም 5.6 ቢሊዮን ሴቶች ሲሆኑ 2.2 ቢሊዮን ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን ጽፈዋል።
ይህን መረጃ ካጋሩና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ካላቸው የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘Gamo ArbaMinch፣ Humbo Press-ሁምቦ ፕረስ እና Ethiopian Wikileakes ኢትዮጵያ ዊኪሊክስ’ የሚል ስም ያላቸው ገጾች ይገኙበታል።
በነዚህ ገጾች ከተጋሩ መረጃዎች መካከል አንዳንዶቹ በመቶዎች በሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው የተጋሩ ሲሆን በርካታ ሐሳብ እና አስተያየትም ተሰጥቶባቸዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ማጣራት ከላይ በተጠቀሱት እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋራው መረጃ አሳሳች እና ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
የአለምን ህዝብ ብዛት በተመለከተ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት በየጊዜው መረጃዎችን ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ወርልዶሜትር መረጃዎችን እንደ ምንጭነት ተጠቅሟል።
በዚሁ መሰረት የሁለቱ ምንጮች መረጃዎች አሁናዊ የአለም ህዝብ ቁጥር 8.2 ቢሊዮን እንደሆነ ይጠቁማሉ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ክፍል ስር የሚገኘው የስነ-ህዝብ ዘርፍ የቅርብ መረጃ የሆነውና እኤአ ሐምሌ 2024 ይፋ የሆነው ሪፖርት እስከ እኤአ 2100 ያለውን የአለም ህዝብ ብዛት ግምት በዉስጡ የያዘ ነው።
ይህ ሪፖርት የ2025 የአለም ህዝብ ብዛት (ግምት) 7.8 ቢሊዮን ሳይሆን 8.2 ቢሊዮን እንደሆነ ጠቅሷል። ከዚህ ዉስጥ 4.09 ቢሊዮን ሴቶች እንዲሁም 4.13 ቢሊዮን ደግሞ ወንዶች እንደሆኑም ተቀምጧል።
በተጨማሪም በአለም ላይ የወንዶች እና የሴቶች ቁጥር ተቀራራቢ ቢሆንም የወንዶች ቁጥር እንደሚበልጥ የተመድ መረጃ ያሳያል።
ይህም በአለማችን ላይ 5.6 ቢሊዮን ሴቶች እና 2.2 ቢሊዮን ወንዶች አሉ በሚል የሴቶች ቁጥር እንደሚበልጥ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።
የተመድ የቅርብ ጊዜ ሪፖረት ቀጥሎ በሚገኘው ማሳፈንጠሪያ የሚገኝ ሲሆን የህዝብ ብዛትን ጨምሮ በርካታ የስነ-ህዝብ መረጃዎች በዉስጡ ይገኛሉ፡ https://population.un.org/wpp/
ትክክለኛ እና ታማኝ ባልሆኑ ምንጮች የሚሰራጩ መረጃዎች ለተሳሳቱ እና ሀሰተኛ መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::