የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ስለ ኢትዮጵያ ባህር በር ጉዳይ ተናገሩት የተባለው ሀሰተኛ መረጃ
ሐምሌ 26፣ 2017
በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ስለ ባህር በር ጉዳይ ከሰሞኑ የተናገሩትን ንግግር እያጋሩ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ሐምሌ 23 እና 24፣ 2017 ዓ.ም ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኬንያ የነበሩ ሲሆን በጉብኝታቸው ማገባደጃ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የባህር በርን የተመለከተ አጭር ንግግር አድርገው ነበር።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ስለ ኢትዮጵያ ባህር በር ጉዳይ የተናገሩት በሚል ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ተመልክተናል።
ይህ መረጃ “ፕሬዝዳንቱ ‘ያቺን ግዙፍ ሀገር ኢትዮጵያን ተመልከቷት… ባህር በር እንድታጣ ተደርጋለች፣ እንዴት አንድ ሀገር የባህር በሩ ተወስዶ ሊለማ ይችላል? ይህ ችግር ካልተፈታ እጅግ ትልቅ አደጋ በቀጠናው ይፈጠራል’ ሲሉ ተናገሩ” የሚል ነው።
ይህን መረጃ ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘ኢትዮጵያዊነት Ethiopiawinet’ የሚል ስም እና ከ290 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ አንዱ ሲሆን የዚህ ገጽ ልጥፍ በርከት ያሉ ሀሳብ እና አስተያየቶችን አስተናግዷል። ከ70 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም መረጃውን መልሰው አጋርተዉታል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ በኬንያ ቆይታቸው “ኢትዮጵያ ባህር በር እንድታጣ ተደርጋለች፣ እንዴት አንድ ሀገር የባህር በሩ ተወስዶ ሊለማ ይችላል? ይህ ችግር ካልተፈታ እጅግ ትልቅ አደጋ በቀጠናው ይፈጠራል” የሚል ንግግር ፈጽሞ አለማድረጋቸውን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።
ይህ ፕሬዝዳንቱ ያልተናገሩት ነገር ግን እንደተናገሩት ተደርጎ የቀረበ መረጃ ሀሰተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ስለ ጉዳዩ ከተናገሩበት አውድ ውጭ በሆነ መልኩ የቀረበ ነው።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ዘመናዊ ኢኮኖሚን ለመገንባት ገበያ እና ምክንያታዊነት (rationalization) አስፈላጊ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ሰሞኑን አንድ አለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ከሚሰራ ሰው ጋር ባደረጉት ውይይት ደቡብ ምስራቅ ኤሽያ የሚገኙ ሀገራት በሙሉ የባህር በር እንዳላቸው ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን እንደ ዩጋንዳ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሩዋንዳ፤ ቡሩንዲ፤ መሀከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፤ ቻድ እና ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የባህር በር አልባ መሆናቸውን፤ የሀገራቱ መሪዎችም ይህን ችግር ለመፍታት እየሰሩ እንዳልሆነ አንስተዋል። ስለሆነም የገበያ ትስስር እና የባህር በር ችግርን መፍታት ለእድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፕሬዝዳንቱ ሙሉ ንግግር በኬንያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ የተጋራ ሲሆን ቀጥሎ የሚገኘውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማዳመጥ ይቻላል፡ https://www.facebook.com/share/v/1MJxisvoS4/?mibextid=wwXIfr
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በኬንያ ቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የተወያዩ ሲሆን ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች አብሮ መስራት የሚያስችሏቸው ስምንት ስምምነቶችን መፈራረማቸውም ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::