የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ኢትዮጵያ ተናግረውታል በሚል በጋዜጠኛዋ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው
ሐምሌ 9፣ 2017
የቀድሞው የዋልታ ቴሌቭዥን ባልደረባ በመሆን ‘እንነጋገር’ በሚል ፕሮግራም ቃለ መጠይቆችን በማድረግ የምትታወቀው ጋዜጠኛ ሳልሳዊት ባይነሳኝ ከሰሞኑ አንድ ቪድዮ ሰርታ ማህበራዊ ሚድያ ላይ ማሰራጨቷን ተመልክተናል።
ጋዜጠኛዋ በዚህ ቪድዮዋ ላይ “አማራ እና ኦርቶዶክስ መጥፋት አለባቸው… እኔ አይደለም ይህንን ያልኩት። በሪቻርድ ኒክሰን ግዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረ ሄንሪ ኪሲንጀር የተባለ በ1972 (እ.አ.አ) ቀዳማዊ ሐይለሥላሴ ሊወርዱ ሁለት አመት ሲቀሩት ለአሜሪካኖች እንደ ምክር (advice) ተጠንቶ ምክረ ሀሳብ ሆኖ ለፕሬዝደንት ፅህፈት ቤት የቀረበ” እንደነበር ስትናገር ይደመጣል።
ይህ ቪድዮ ከጋዜጠኛዋ አካውንት ውጪ በበርካታ ሌሎች ገፆች የተጋራ ሲሆን በርካታ ግብረ-መልስ አግኝቷል (አንድ ማሳያ: https://www.facebook.com/share/v/1Hs79wzRrx/)
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ በርከት ያሉ ዶክመንቶችን የተመለከተ ሲሆን የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ (Secretary of State) የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር ‘አማራ እና ኦርቶዶክስ መጥፋት አለባቸው’ የሚል ንግግር እንዳልተናገሩ ማየት ችለናል።
በመጀመርያ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ህይወታቸው ያለፈው እና እ.አ.አ ከ1973 እስከ 1977 የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኪሲንጀር ጋዜጠኛ ሳልሳዊት እንዳለችው እ.አ.አ በ1972 የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ካውንስል ሀላፊ እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልነበሩም።
ኪሲንጀር በርካታ ንግግሮችን በኢትዮጵያ ዙርያ አድርገው እንደነበር ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ለምሳሌ ቲዎዶር ኤም ቬስታል የተባሉ የታሪክ ፀሀፊ ‘Abren’ በተባለ ድረ-ገፅ ላይ እንደፃፉት ኪሲንጀር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዘር፣ የሀይማኖት እና ሌሎች ክፍፍሎችን በመጠቀም በአፄ ሐይለሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ ድጋፍ እየተስፋፋ የነበረውን የፓን-አፍሪካን ንቅናቄ ለማዳፈን ጥረት አድርገው ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ውጥረት ተይዛ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነፃት ምሳሌ መሆን እንዳትችል የታቀደ እንደነበር የታሪክ ፀሀፊው ያስረዳሉ። ይህ አካሄድ በአሜሪካው ‘National Security Study Memorandum 200 (NSSM 200)’ ላይ ተቀምጦ እንደሚገኝ ፀሀፊው ጠቁመዋል።
ነገር ግን እነዚህ የፀሀፊው መረጃዎችም እስካሁን የአሜሪካ መንግስት በየወቅቱ በሚለቃቸው (declassify በሚያረጋቸው) ቆየት ያሉ ዶክመንቶች ላይ እንዳልተገኘ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይልቁኑ ኪሲንጀር በወቅቱ ኢትዮጵያን የሶቪየት ህብረትን የመስፋፋት አጀንዳ መግቻ አጋር ሀገር አድርገው ለአፄው ስርዐት በርካታ ወታደራዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ያገላበጥናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
እንደ አሜሪካ ያሉ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሃገራት ውስጥ ያሉ ክፍፍሎችን በመጠቀም የራሳቸውን አጀንዳ የማሳካት ፍላጎት እንዳላቸው በርካታ ታሪካዊ ምሳሌዎች ቢጠቁሙም የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት በቀጥታ ‘አማራ እና ኦርቶዶክስ መጥፋት አለባቸው’ ብለው የተናገሩት ንግግር እንደሌለ ማረጋገጥ ችለናል።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::