ከአሳሳች የፕሮፋይል ምስሎች እስከ ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት: በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረኩ ምስሎች የፈጠሩት ስጋት
መስከረም 18፣ 2017 ዓ.ም
በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የሚፈበረኩ እና ከትክክለኛ የሰው ምስል ለመለየት አዳጋች የሆኑ ምስሎች ብዛት እና ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ሰው መሰል ፊቶች ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር አካውንቶችን እና ገጾችን ለመክፈት፤ ሀሰተኛ መረጃን ለማሰራጨት፤ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመፈጸም፤ ግለሰቦች እና ተቛማት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንዲሁም የተቀናጁ የመረጃ ዘመቻዎችን ለማካሄድም ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎች ታማኝነት ላይ የራሳቸውን ፈተናዎች መደቀናቸውንም በያዝነው እኤአ 2024 በአሜሪካ በሚገኙት ኢንዲያና እና ኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የተደረገ ጥናት ይጠቁማል።
ጥናቱ በየቀኑ 10 ሺህ የሚሆኑ እና በሰው ሰራሽ አስተዉሎት የተፈበረኩ ምስሎችን የፕሮፋይል ምስል ያደረጉ የኤክስ (ትዊተር) አካውንቶች የመረጃ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይገልጻል።
በተጨማሪም ጥናቱ ‘እነዚህ አካውንቶች ለማጭበርበር ጥቅም ላይ የሚዉሉ ሀሽታጎችን እና ማስፈንጠሪያዎችን ያጋራሉ፤ በተወሰኑ አካውንቶች የሚጋሩ መረጃዎችን አጋነው ያሰራጫሉ እንዲሁም ቻት ጂፒቲን (ChatGPT) በመጠቀም የተለያዩ ይዘቶችን ጽፈዉ ያጋራሉ’ ይላል።
ከነዚህ አካውንቶች መካከል አንዳንዶቹ የትክክለኛነት ማረጋገጫ (Verification badge) ያላቸው መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገውም በጥናቱ ተጠቅሷል።
የዴቪድ ግሪን (David Green) ጉዳይ
ኢትዮጵያ ቼክ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ባደረገው ምልከታ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረኩ ምስሎችን እንደ ፕሮፍይል ምስል የሚጠቀሙ፤ ስማቸው በብዛት የምዕራቡ ሀገራት ዜጎች የሆነ የሚያጋሯቸው መረጃዎች ግን ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ የሚያተኩሩ አካውንቶችን ተመልክቷል።
ከነዚህ መካከል ደግሞ ‘David Green’ የሚል ስም ያለው እና ምስሉ የሚታየው አካውንት አንዱ ነው።
ይህ የኤክስ (ትዊተር) አካውንት እኤአ በ2014 የተከፈተ ሲሆን እኤአ ከ2015 ወዲህ የተለያዩ መረጃዎችን በንቃት ሲያጋራ ቆይቷል።
ይህ አካውንት ‘David Green’ የሚል ስም እና የነጭ ሰው ፕሮፋይል ምስል ይኑረው እንጂ የሚያጋራቸው መረጃዎች ግን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ከሶማሊላንድ ጋር የተገናኙ ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የባሕር በርን በተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን የተመለከቱ መረጃዎችን በስፋት እያጋራ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በአካውንቱ ላይ ባደረገው ማጣራት አካውንቱ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት የተሰራ የፕሮፋይል ምስልን አሳሳች በሆነ መልኩ ይጠቀማል። ይህ በ ‘AI’ የተሰራ ምስልም በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://www.deviantart.com/canadianai/art/AI-Generated-White-Canadian-Businessman-951803757
በተጨማሪም የአካውንቱ ሀንድል (twitter handle) በተለያዩ ጊዜያት ሲቀያየር እንደነበረም ማረጋገጥ ችለናል። ለምሳሌ ያክል እኤአ በ2019 አካውንቱ ‘@Alfie_Ismail’ የሚል ሀንድል ይጠቀም ነበር።
እነዚህ ጉዳዮች አካውንቱ ከሚያጋራቸው ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ መረጃዎች ጋር ተደምሮ የአካውንቱን ትክክለኛነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው።
ምን ማድረግ አለብን?
የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረኩ ምስሎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።
ኤክስ በበኩሉ ኮምፒተርን በመጠቀም የተመረቱ ምስሎችን በመጠቀም ሌላ በእዉን የሌለ ሰውን መስሎ የማህበራዊ ትስስር ገጹን መጠቀም እንደ ማታለል እንደሚቆጠር ይገልጻል።
ይህ እንዳለ ሆኖ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረኩ ምስሎችን እንደ ፕሮፍይል ምስል የሚጠቀሙ አካውንቶች ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም ለመጭበርበር ሊዳርጉን ስለሚችሉ መሰል አካውንቶችን በጥንቃቄ መመልከት እንዳለብን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በዚህ ረገድ የመጀመሪያው እርምጃ ደግሞ አንድ ማንነቱ በማናውቀው አካውንት የተሰራጨን መረጃ አምነን ከመቀበላችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት የአካውንቱን ባለቤት ማንነት እና መረጃው የተጋራበትን አላማ ማወቅ ያስፈልጋል።
የአካውንቱን ባለቤት ማንነት ለማወቅ ደግሞ ስሙን እና የፐሮፋይል ምስሉን መመልከት አብዛኞቻችን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው።
አንድ የፕሮፋይል ምስል ትክክለኛ የሰው ምስል ነው ወይስ በሰው ሰራሽ አስተዉሎት (AI) የተፈበረከ ነው የሚለዉን ለመለየት በቅድሚያ የመስሉን ይዘት እና በዉስጡ ያሉ ስህተቶችን ለማወቅ መሞከር ይመከራል።
ምንም እንኳን በሰው ሰራሽ አስተዉሎት የተመረቱ ምስሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉና ለመለየት አስቸጋሪ እየሆኑ የመጡ ቢሆንም ምስሎቹን በትኩረት መመልከት ስለ ትክክለኛነቱ ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል።
ከዚህ ባለፈ ደግሞ አንደ ጉግል ኢሜጅስ፤ ቢንግ፤ ያንዴክስ እና ቲንአይ የመሳሰሉ ምስልን በምልሰት ለመፈለግ የሚረዱ መገልገያዎችን በመጠቀም ምስሉን በምልሰት በመፈለግ ከዚህ በፊት የት እና ለምን ጠቅም ላይ ውሎ እንደነበር ማጣራት እንችላለን።
በተጨማሪም የማህበራዊ ትስስር ገጹን ወይም አካዉንቱን ስም (username)፤ ሀንድል፤ ህይወት ታሪክ (Bio) እንዲሁም የሚያጋራቸውን መረጃዎች በመመርመር የትክክለኛ ሰው መሆኑን ማጣራትም ይመከራል።
የአካውንቱ ተከታዮች ማንነት እና አካዉንቱ ከተከታዮቹ ጋር ያለው መስተጋብርም ስለ አካውንቱ ትክክለኛነት ፍንጭ ሊሰጡን የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::