የተጣራ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት እና መረጃ ለማጣራት የሚጠቅሙ የጎግል መገልገያዎች

ነሐሴ  23፣ 2016

ጎግል ለብዙሃኑ የተጣራ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት እንዲሁም ለመረጃ አጣሪዎች፣ ለጋዜጠኞች እና ለተመራማሪዎች መረጃን ለማጣራት የሚያግዙ በርካታ መገልገያዎች አሉት። ከነዚህም መካከል የጎግል ፋክት ቼክ ኤክስፕሎረር፣ ጎግል ፋክት ቼክ ሌብል እና ጎግል ስኮላር ይጠቀሳሉ።

እነዚህ መገልገያዎች የተጣራ መረጃን ከመረጃ አጣሪዎች በቀላሉ ለማግኘት፣ የተጣራ መረጃን ለመለየት እንዲሁም መረጃን ለማጣራት የሚያግዙ ናቸው። ከእኛ ሀገር አውድ አኳያ ከላይ የተጠቀሱት መገልገያዎች በተለይም አለም አቀፍና ቀጠናዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ለማሰስ በይበልጥ ልንጠቀምባቸው እንችላለን።

ጎግል ፋክት ቼክ ኤክስፕሎረር (Google Fact Check Explorer): ይህ መገልገያ በመረጃ አጣሪ ተቋማት ተፈትሸው የተጋሩ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት የሚረዳ ነው። ወይም የተጣሩ መረጃዎች ማሰሻ ልንለው እንችላለን። መገለገያው በተለይም ለጋዜጠኞች እና ለተመራማሪዎች ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ መረጃ አጣሪዎች ያጋሯቸውን ይዘቶች ካለቡ ውጣውረድ ለማግኘት ያስችላል።

መገልገያውን ለመጠቀም ቀዳሚ የሚሆነው የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ መከተል ነው: https://toolbox.google.com/factcheck/explorer/search/list:recent;hl=en ቀጥሎም በመረጃ አጣሪ ተቋማት ተጣርቶ ይሆን ወይ ብለው ያሰቡት ጉዳይ ወይም ምስልን በመፈልጊያ ሳጥኑ ውስጥ ያስቀምጣሉ። ከዚያም የተጣራው መረጃ የጊዜ ቀደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ የሚቀርብልዎ ሲሆን መረጃውን ያጣራውን ተቋም ስምና ብያኔም መመልከት ይችላሉ። በመጨረሻም ከቀረበልዎት ዝርዝር የፍለጋ ውጤት መካከል እየመረጡ ማንበብ ይችላሉ።

ጎግል ፋክት ቼክ ሌብል (Goole Fact Check Lable): የጎግልን መፈለጊያ ተጠቅመን መረጃ ስናስ ስ የምንፈልገው ጉዳይ ወይም ምስል በመረጃ አጣሪ ተቋማት የተጣራ ከሆነ ጎግል በውጤቱ ግርጌ ይህንኑ ይነግረናል። ጎግል ከሚነግረን መረጃዎች መካከል መረጃውን ያጣራውን ተቋም ማንነት፣ ብያኔ እንዲሁም የተጣራውመረጃ ቅምሻ ይገኙበታል። በፍለጋ ውጤቶች ግርጌ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ከተመልከትን ወደ ውስጥ በመግባት የተጣራውን መረጃ መመልከት ይጠቅመናል።

ጎግል ስኮላር (Google Scholar): ይህ በጎግል የፍለጋ አገልግሎት ስር የሚገኝ መገልገያ በሳይንሳዊ ስነዘዴን በመጠቀም በባለሙያዎች ተገምግመው (peer-reviewed) ያለፉ የምርምር ውጤቶችን ያቀርባል። ይህም የተጣራ መረጃ ለማግኘት በእጅጉ የሚጠቅም መገልገያ ነው።

የተጣራ መረጃን በቀላሉ ለማግኘት እና መረጃ ለማጣራት ስለሚጠቅሙ መገልገያዎች በማወቅ እራሳችንን ከሀሠተኛና ከተዛቡ መረጃዎች እንጠበቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::