ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ከአፍሪካ 2ደረጃ ሆነች በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው

ጥቅምት 01 2017 ዓ.ም

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ሚድያዎች፣ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች “ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ሆነች” የሚል መረጃ አጋርተዋል።

ይህን መረጃ ያጋሩት ሚድያዎች እና ግለሰቦች እንደ መረጃ ምንጭነት የተጠቀሙትም ኢን ኦን አፍሪካ (IOA) የተሰኘ ድረ-ገጽ ነው፡ https://www.inonafrica.com/ 

ይህ በደቡብ አፍሪካ እአአ በ 2007 ዓ/ም የተመሰረተ ተቋም በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቅ ነው።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ እየተሰራጨ የሚገኘውን መረጃ በተመለከተ የኢን ኦን አፍሪካን ድረ-ገጽን እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር ገጾቹን የተመለከተ ሲሆን የተባለው ሪፖርት በድርጅቱ የመረጃ ቋቶች ላይ እንደሌሉ አረጋግጧል።

እየተጋራ በሚገኘው ስክሪን ቅጂው የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኙ ጽሁፎች እና ምስሎች ከተቋሙ ትክክለኛ ድረ-ገጽ ጋር ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም ሪፖርቱ ግን ትክክለኛው የ ‘IOA’ ድረ-ገጽ ላይ እንደሌለ አረጋግጠናል።

በተጨማሪም ከመረጃው ጋር እየተጋራ የሚገኘው የስክሪን ቅጂ የፊደል አቀማመጥ/ፎንት ስህተቶች የሚታዩበት መሆኑንም ተመልክተናል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መረጃውን በፌስቡክ ገጹ ካጋራ ከሰዓታት በኋላ መልሶ ማጥፋቱንም ተመልክተናል።

ከሰሞኑ ተመሳስለው የተዘጋጁ ሀሰተኛ ስክሪን ቅጂዎች በስፋት እየተሰራጩ እና በርካቶችን ለስህተት እየዳረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም መሰል ስክሪን ቅጂዎችን አምነን መረጃዎችን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::