ከትናንት በስቲያ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሰማው ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ምንድን ነበር?

ነሐሴ 07፣ 2016 ዓ.ም

በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ከጅማ እስከ ወለጋ እንዲሁም እስከ ወላይታ ድረስ ከፍተኛ ድምፅ እንደሰሙ ባለፉት ሁለት ቀናት መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። አንዳንዶችም መሬት ላይ ወድቆ አገኘነው ያሉትን ምስል ሲያጋሩ ነበር።

በዚህ ፍንዳታ ዙርያ የተለያዩ አስተያየቶች እና ግምቶች የተሰጡ ሲሆን አንዳንዶች የከባድ ጦር መሳርያ ድምፅ ነው፣ ሌሎች መብረቅ ነው እንዲሁም የተወሰኑት ከሰማይ የወደቀ ነገር አለ ሲሉ ተመልክተናል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ በጠፈር ሳይንስ እና ጂኦስፓሺያል ኢንስቲትዩት የአስትሮፊዚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ዶ/ር ሰለሞን በላይን አነጋግሯል።

“ከተመለከትኳቸው ምስሎች መረዳት የቻልኩት ወደቁ የተባሉት አካላት የሚቲዮራይት ስብርባሪ መሆናቸውን ነው” ያሉት ዶ/ር ሰለሞን የጅማ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ዲፓርትመንትን በዚህ ዙርያ እንዳናገሩና ተመሳሳይ ምላሽ እንዳገኙ ለኢትዮጵያ ቼክ አስረድተዋል።

ወድቆ የተገኘው አካል ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ለምርመራ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

“ይህ ከፍተኛ ድምፅ የተሰማው ከደቡብ እስከ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ድረስ ነው፣ አጋሮ አካባቢ አንዳንድ ስብርባሪ ተገኝቷል” ብለዋል።

ዶ/ር ሰለሞን በአሁኑ ወቅት የአለም አቀፈ አስትሮኖሚካል ህብረት ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::